ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህዝብን መሠረት አድርገው በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህዝብን መሠረት አድርገው በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ድሬደዋ ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ አመታት ህዝብን መሠረት አድርገው በተሰሩ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በድሬዳዋ አስተዳድር የብልጽግና ፓርቲ ምስረታ 5ተኛ ዓመት ክብረ በዓል የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ዛሬ በፓናል ውይይት ተካሄዷል።
የፓናል ውይይቱን የመሩት የብልጽግና ፓርቲ ዋና ፅህፈት ቤት የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደናገሩት፤ ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ህዝብን መሠረት አድርጎ ባከናወናቸው ተግባራት የተገኙ ውጤቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በተጨማሪም ፓርቲው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፓለቲካው፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በፍትሃዊነትና በእኩልነት ተሳትፎ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ እየተጋ ከመሆኑም ባሻገር በዲፕሎማሲ መስክም ውጤታማ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የለውጡ ዓመታት ክዋኔዎች አበረታች ውጤቶች የተመዘገበባቸውና የብልፅግና ጉዞን ስኬታማነት እያረጋገጡ መሆናቸውን ገልፀው እነዚህ ጅምር ውጤቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትጋት፣ በፍጥነትና በፈጠራ የታገዙ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የፓናል ውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባና የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ ድሬዳዋ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን በመተግበር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተሰሩ ስራዎች የአገራዊ ብልጽግናን አይቀሬነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በቀጣይም የተገኙ ውጤቶችን ለማደፍረስና በዜጎች መካከል ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን ለህግ በማቅረብ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ በላቀ ደረጃ ለማሳካት መረባረብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ወጥ አገራዊ ፓርቲ በመመስረት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለተፅዕኖዎች የማትበገር አገር የመገንባት ሂደትን እያሳካ ይገኛል ያሉት ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ ባለፉት አምስት ዓመታት የተቋማት እና የአሠራር ሪፎርም በማካሄድ የህዝብን የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ የመመለስ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል።
በተጨማሪም በትምህርት፣ በጤና፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ የኑሮ ውድነትን በማቃለል፣ የኮሪደር ልማትን በመጀመር የብልጽግና ትልሞችና ግቦች በተሻለ ውጤት እንዲጓዙ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት በየደረጃው የሚገኙ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮችና አባላት በቀጣይ የተስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረባረቡም አስታውቀዋል።