ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተላቃ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግብ አድርጓል

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት አምስት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዘርፈ ብዙ ችግር ተላቃ የዜጎቿን ተጠቃሚነትና ብሔራዊ ፍላጎቶቿን በማረጋገጥ ረገድ አመርቂ ውጤት እንድታስመዘግብ ማድረጉን ገለጸ።

የብልፅግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን በፌዴራል ተቋማት ደረጃ የተከበረ ሲሆን "የሀሳብ ልዕልና ለሁለንናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

ከፖናሊስቶች መካከል የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የፌዴራል ተቋማት የብልፅግና ፓርቲ አስተባባሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ብልፅግና ፓርቲ እንዲወለድ ምክንያት የሆነው ከለውጡ በፊት የነበሩ ስብራቶች ናቸው ብለዋል።

በለውጥ ሂደት የተፀነሰ እና ለውጡን የመራ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የተከፋፈለና በውጥረት የተሞላ ፖለቲካ፣ነጠላ ትራክቶች ጫፍ የደረሱበት እንዲሁም ሰብዓዊና የዲሞክራሲ መብቶች ጥሰት የወለደው ህዝባዊ ቁጣ ኢትዮጵያን መስቀለኛ መንገድ ላይ አድርጓት እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት በወቅቱ የነበረው ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ መታደስ አለበት የሚሉና ጠጋግኖ ማስቀጠል በሚሉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ፍትጊያ እንደነበር አስታውሰው፣ በዚህ መሀል የአመራር ሽግሽግ እንዲደረግ ማስገደዱን ይህም በሂደት ለውጡን መውለዱን አስታውሰዋል።

በመደመር እሳቤ የቀጠለው ሀገራዊ ለውጡ ደግሞ ብልፅግና ፓርቲን እንደወለደ ተናግረዋል።

በ5 ዓመታት ውስጥ ሀገርን ከመስቀለኛ መንገድ የመለሱ እርምጃዎች መወሰዳቸውን አስታውሰው፣ ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመጀመሪያ ዕለት የፓርላማ ንግግር እንደ ማህበራዊ ውል የሚወሰድ ነው ብለዋል።

ለውጡ የፖለቲካ ምህዳር የሰፋበት፣ የሚዲያ ነፃነት የተረጋገጠበት፣ የሕግ ማሻሻያና የተቋማት ሪፎርሞቾ የተደረጉበትና የዲሞክራሲ ምህዳር የሰፋበት ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ብልፅግና አካታችና አሰባሳቢ ሆኖ የመሀል ፖለቲካ መንገድን በመከተል የትርክት መዛባት እንዲስተካከል መሰረት የተጣለበት እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት መፍጠር የሚያስችል የትርክት ግንባታ ሂደት የተጀመረበት፣ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበትና የሽግግር ፍትህ ሂደት የተጀመረበት እንደሆነም እንዲሁ።

በጥቅሉ ለውጡ ሀገርን ከመስቀለኛ መንገድ ያሻገረ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ዛሬም ግን በሀሳብ የበላይነት የሚመራ ትውልድ ግንባታ ላይ አበክሮ መስራት እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።

ሰላም ማረጋገጥ፣ አሰባሳቢ ትርክት ግንባታን ማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት ስራዎችን በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የፓርቲው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ አህመድ ሽዴ የኢኮኖሚ ስብራቶችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት፤ ከለውጡ በፊት ዘላቂ የኢኮኖሚ ሞዴል መከተል ባለመቻሉ የዋጋ ግሽበት የገነነበት፣ የዕዳ ጫና የተቆለለበት፣ የግሉ ዘርፍ የተገለለበት፣ ኢፍትሐዊ ኢኮኖሚ እና ተያያዥ ችግሮች ተደማምረው የማክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ ለማስከተል አደጋ የደቀኑበት ወቅት እንደነበር አውስተዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ከማክሮ ኢኮኖሚ የፋይናንስ ቀውስ ሀገርን የታደገ እና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።

የ10 ዓመት የኢኮኖሚ መርሐግብር የተቀረፀበት እና የዕዳ ስጋቶች የተቃለሉበት፣ የዋጋ ንረት መቆጣጠር የተቻለበት እና ኢንቨስትመንት የተስፋፋበት እንደሆነ አብራርተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ ዘመን የብዝሃ ኢኮኖሚ ስርአት ላይ ትኩረት በመደረጉ ባለፉት ዓመታት በአማካይ 7 ነጥብ 2 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መመዝገቡን ጠቅሰዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መደረጉ ኢኮኖሚውን ዘላቂና ተወዳዳሪ ለማድረግ አይተኬ ሚና እንደተጫወተም እንዲሁ።

የፖለቲካ ኢኮኖሚው በቀጣናው ግዙፍ መሆኑን ገልፀው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሙ ለዕድገት ምቹ የሆነ፤ የዕዳ ጫና ያቀለለ፣ ዕድገቱም ዘርፈ ብዙ የሆነ እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ያሻሻለ ነበር ብለዋል።

ጠንካራ የዕድገት መሰረት የተጣለበት በመሆኑ ለዘላቂነቱ በቀጣይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስተመንት ማስፋፋት፣ የሀገር ውስጥ ገቢ ማሳደግ፣ ሀገራዊ ባለሀብቶችን መደገፍ እንዲሁም የወጪ ምርት ዕድገት ማሳደግ ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለዚህ ደግም ምቹ የሰላም ሁኔታ፤ የመፈፀም አቅም፣ የፐብሊክ ፋይናንስ ማጎልበት እና ከውጭ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) ማሳደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በጥቅሉ ኢኮኖሚው ዘመናዊና ተወዳዳሪ ሆኖ የሚቀጥል ተስፋ ያለመለመ መሆኑን ገልፀው፤ዘላቂ፤ አሳታፊና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማምጣት የሁሉንም አካላት ትብብር ይጠይቃል ነው ያሉት።

የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው በማህበራዊ መስኮች የተመዘገቡ ድሎችና ስኬቶችን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ የማህበራዊ ልማት አካታችነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ እንደነበር ገልፀዋል።

የሀሳብ መሸራረፍና እጥረት የሌለበት በመሆኑ ሁሉን አቀፍ ብልፅግና ለማረጋገጥ በድህነት ቅነሳ፣ በጤና ልማትና በትውልድ ግንባታ ትልልቅ ድሎች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን በተሰሩ የሪፎርም ስራዎች ጥራትና አካታችነት መሰረት ያደረገ የትምህርት ስርዓት መገንባቱን ጠቅሰዋል።

ከቅደመ መደበኛ ጀምሮ አዲሲቷ ኢትዮጵያን መሸከም የሚችል ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።

ከጤና ስርዓት አኳያ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ጨምሮ ዘርፉ ዘመኑን እንዲዋጅ መደረጉን መከላከል ብቻ ሳይሆን አክሞ ማዳን መቻሉን፣ የእናቶች ጤናና ሕይወት ያሻሻለ ለውጥ መሆኑን ተናግረዋል።

ከማህበራዊ ጥበቃ አኳያም የአረጋውያንና አቅመ ደካሞችን ሕይወት ለማሻሻል የተሰሩ ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ በድህነት ቅነሳ ላይ ትኩረት ያደረጉ ስራዎች መከናወናቸውን፣ብዝሀነትን ማዕከል ያደረጉ የባህል ልማት ስራዎች መከናወናቸውን በማንሳት ሴቶች እና ወጣቶች ተጠቃሚ ያደረጉ ድሎችን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

ብቁ፣ አምራች እና በስነ ምግባር የታነፀ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የተጀመሩ ስራዎች ለአብነትም ክህሎትን መሰረት ያደረገ የስራ ፈጠራ ፖሊሲ መቀረፁ፣ ስነ ምግባር የትምህርት ስርዓት አካል መደረጉ፣ ድህነትን የሚጠላ አምራች ዜጋ ለመፍጠር የተጀመረው ስራ ፍሬ እያፈራ እንደሆነ ነው ያነሱት።

በመሰረተ ልማት ስራዎችም በአረንጓዴ ፓርኮች እና በኮሪደር ልማት ስራዎች አካታች እና ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ ማህበራዊ ልማት መሰረት ያደረጉ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።

የሀገረ መንግስትና የብሔረ መንግስት ግንባታ ረገድ በተለይም ከነጠላ ትርክት ወደ አሰባሳቢ ትርክት መሻገርና ሰው ተኮር ተጨባጭ ውጤቶችን ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የተፈጠረው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዘርፈ ብዙ ትሩፋቶች እያስገኘ በመሆኑ አጓጊ ጅምሮችን ከዳር ለማድረስ የሁላችንንም ቅንጅት ይጠይቃል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው በዲፕሎማሲው መስክ የተገኙ ስኬቶችን አብራርተዋል።

የውጭ ግንኙነት ስራዎች በብልፅግና ዘመን ሀገራዊ ክብርና ብሔራዊ ጥቅም እንዲሁም የዜጎችን ክብር ማዕከል ያደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

የሀገር ውስጥ አቅምን ለማጠናከር የተሰሩ ስራዎች ለውጪ ግንኙነት መሰረት እና አንኳር ተግባራት መሆናቸውን ገልፀው፣ ዓለም አቀፍና አካባቢው ትብብርና ትስስር የሚያጠናክሩ ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በቀጣናዊ ትብብር፣ በሰላምና ደህንነት ስራዎች ረገድ በ5 ዓመታት አኩሪ እና የኢትዮጵያን ከፍታ ያረጋገጡ የውጭ ግንኙነት ስራዎች መከናወናቸውንም ጠቁመዋል።

በጎረቤት ሀገራት ሰላም እንዲሰፍን የተሰሩ ስራዎችም የተረጋጋ አህጉር እንዲፈጠር ያገዙና ዓለም አቀፍ ዕውቅና የተቸራቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጥ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መተግበሩን ገልፀው፤ ደፋር እና በብሔራዊ ጥቅም ላይ የማይደራደር የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ እየተከተልን ነው ብለዋል።

ውስጣዊ ግጭት ለማስቆም የተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት፣ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በመሰረተ ልማት የመተሳሰር ስራዎች፣ በውሃ ዲፕሎማሲ በተለይ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የነበረውን የኢ-ፍትሀዊነት ስብራት የተጠገነበት፣ የብድር አቅርቦትን ጨምሮ ከፋይናንስ ተቋማት ጋር የተፈጠሩ አጋርነቶች እንዲሁም የውጪ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገት የብልፅግና ዘመን የዲፕሎማሲ ድል ማሳያዎች እንደሆኑ ገልፀዋል።

ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በቀጣናው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን መቻሉንም እንዲሁ።

የዓለም የጂኦ ፖለቲካ ውድድር ለአብነትም የቀይ ባህር እና የአፍሪካ ቀንድ ቀውስ ቁልፍ ፈተናዎች እንደሆኑ በመጥቀስ ፈተናዎችን ተቋቁሞ በማለፍ ደፋር የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን አንስተዋል።

ከሁኔታዎች ጋር የሚራመድና ለብሔራዊ ጥቅም የወገነ ዲፕሎማሲ መተግበሩን በመጥቀስ፣ የምዕራብም የምስራቅም ጎራ የወገነ ሳይሆን ጥቅምን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም