ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየሰራች ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየሰራች ያለው ሥራ የሚበረታታ ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየሰራች ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን ዓለም አቀፉ የትራንስፖርትና ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ትናንት የተከፈተው የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም ዛሬም ቀጥሏል።
የዚሁ አካል የሆነው ሲምፖዚየም በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ሲሆን በኢትዮጵያ አረንጓዴ ትራንስፖርት አሁናዊና የቀጣይ ትግበራ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።
በመድረኩ የዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩትና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ (ማኑዋል) ይፋ ሆኗል።
የኢንስቲትዩቱ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ክሪስ ኮስት፤ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን አቅም በመቀጠም አረንጓዴ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋት የጀመረቻቸው ጥረቶችም አድንቀዋል።
መንግሥት በትላልቅ የመንገድ ግንባታ ላይ እያካሄደ ያለው ኢንቨስትመንት ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ያለው ሚና የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ትራንስፖርት ለሚሳተፉ ባለኃብቶች ምቹ መዳረሻ መሆኗን ጠቅሰው፣ ይህን ዕድል በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን በሁሉም አካባቢዎች ማዘመንና ማስፋት ይገባል ብለዋል።
ዛሬ ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ የከተሞችን የኮሪደር ልማቶችን እንዲሁም የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
መመሪያው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሳይክልና የእግረኛ መንገድ በማስፋት የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥና ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ፤ ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የአረንጓዴ ስትራቴጂ ነድፋ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዘርፉ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያስችሉ ተጨባጭ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ ጎሳዬ መንግሥቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው በኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም አረንጓዴ ልማትን ማረጋገጥና የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል በልዩ ትኩረት እየተሰራበት ነው።