ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ የፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ወደ ስራ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

ኢኒስቲትዩቱ ዓለም ላይ ላሉ የፖሊስ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም የማጠቃለያ፣የዕውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም ዛሬ በሰንደፋ ከተማ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዩኒቨርሲቲው በአፍሪካ ግንባር ቀደም የፖሊስ ተቋማት ደረጃን ያሟላና የጥናትና የምርምር አቅሙን በማሳደግ ዘመኑን የሚመጥን የምርመር አቅም የሚያጎለብት የፎረንሲክ ምርመራና የምርምር ልህቀት ማዕከል ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው በ1939 ዓ.ም ቢቋቋምም እንደ አንጋፋነቱ በሚፈለገው ደረጃ እድገት ሳያሳይ መቆየቱን አስታውሰዋል።

በለውጡ መንግስት በተደረገለት ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ሀገራት ጭምር የስልጠና እና የምርምር ማዕከል የመሆን አቅም የፈጠረ ተቋም መሆን እንደቻለ ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲው ዘመኑን የሚመጥን የፖሊስ የስልጠና ተቋም እንዲሆን ዓለም አቀፍ የፖሊስ ሊደርሺፕ ኢንስቲቲዩት ግንባታ በቅርቡ ሲጠናቀቅ ዓለም ላይ ላሉ የፖሊስ ተመራማሪዎች የምርምር ማዕከል ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በስትራቴጂው አማካኝነት በለያቸው የትኩረት መስኮች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት በትምህርትና ስልጠና፣ በምርምር፤ በማማከርና በማህበረሰብ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በአስተዳደራዊ ዘርፎችም ውጤታማ ተግባራቶችን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የፎረንሲክ ሳይንስ ምርመራ እና የምርምር ኢንስቲትዩት የልህቀት ማዕከል ተጠናቆ ሥራ እንዲጀምር ላደረጉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ማኔጅመንት አባላት ምስጋና አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በ2016 ዓ.ም በጀት አመት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እቅድ አፈፃፀም የተሻለ እንዲሆን የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተቋማትና ግለሰቦች እውቅናና ሽልማት እንደተበረከተላቸው ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም