ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ያላቸውን ልምድና የትብብር ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ደቡብ አፍሪካ በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ያላቸውን ልምድና የትብብር ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ገለጹ
አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ በሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ ያላቸውን ልምድና የትብብር ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ከደቡብ አፍሪካ አቻ ተቋማት ጋር ትብብር መፍጠርን አላማ ያደረገ ጉብኝት አካሒዷል።
የልዑካን ቡድኑ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሲቪል ሰርቪስ ቢሮ ኃላፊዎች እና የኮሚሽኑ ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።
ልዑኩ ከደቡብ አፍሪካ የብቃት ባለሥልጣን፣ ከፐብሊክ ሰርቪስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ የመንግስት ትምህርት ቤት፣ ከፐብሊክ ሰርቪስ መምሪያ ተወካዮች ጋር ውይይት ያደረገ ሲሆን የተቋማቱን የስራ እንስቃሴም ጎብኝቷል።
በተጨማሪም በሶዌቶ የሚገኘውን የ”Maponya Urban Mall Sosong” የተሰኘ ሰርቪስ ማዕከልንም ተመልክቷል።
በስራ ጉብኝቱ ወቅት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው የለውጥ ስራ ገለጻ አድርጓል።
የደቡብ አፍሪካ ተቋማት በሲቪል ሰርቪስ ሴክተር ማሻሻያ እና ልማት ላይ በትብብር ለመስራት እንደሚፈልጉና በአቻ ተቋማት መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን በፕሪቶሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።