ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ የትራፊክ ሕጎችን በመተግበር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ኅብረተሰቡ የትራፊክ ሕጎችን በመተግበር የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ገለጸ።

የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ቀን ዛሬ በአዲስ አበባ ተከብሯል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ከ1 ሚሊየን በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት መረጃ ያሳያል።

ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችም በትራፊክ አደጋ ምክንያት ለቀላልና ለከባድ የአካል ጉዳት ተጋላጭ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክበበው ሚዴቅሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የትራፊክ ሕጎችን በመተግበር የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።


 

ባለሥልጣኑ የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመከላከል የተለያዩ የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያ ሥራዎችንና የመፍትሄ እርምጃዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም የእግረኛን ደኅንነት ማሻሻል እንዲሁም አደጋ የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ ምህንድስና ማሻሻያዎችን የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በግንዛቤ ማስጨበጫ የታገዙ የትራፊክ ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው መርኃ ግብር የደም ልገሳና ለተጎጂ ቤተሰቦች ድጋፍ በማድረግ ታስቦ ውሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም