ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ ይፋ ሆነ 

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦  የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ ይፋ ሆነ። 

ትናንት የተከፈተው የኢትዮ-ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም ዛሬም ቀጥሏል።

የዚሁ አካል የሆነው ሲምፖዚየም በዛሬው ዕለት እየተካሄደ ነው። 

በመድረኩ የዓለም አቀፉ ትራንስፖርት ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩትና የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያ (ማኑዋል) ይፋ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ከተሞች የመንገድ ዲዛይን መመሪያው የከተሞቹን የኮሪደር ልማቶችን እንዲሁም የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።  

መመሪያው የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሳይክልና የእግረኛ መንገድ በማስፋት የተሳለጠ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል። 


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዘላቂ የአረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋት እየሰራች ነው።

ዓለም አቀፋዊ ተግዳሮት የሆነውን የአየር ብክለትን ለመከላከል በታዳሽ ኃይል የሚሰሩ የትራንስፖርት አማራጮችን መጠቀም ይገባልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል በመጠቀም የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን የአረንጓዴ ስትራቴጂ ነድፋ በትኩረት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።  

የብዙኃንና የሳይክል ትራንስፖርትን ከማስፋት ጎን ለጎን ምቹ የእግረኛ መንገዶችን በመገንባት ጤናማ ዜጋ እንዲፈጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም