የህክምና ተመራቂዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ሊተጉ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የህክምና ተመራቂዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ሊተጉ ይገባል
ሀዋሳ ፤ ህዳር 14/2017 (ኢዜአ):- የህክምና ተመራቂዎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ጤናማ አምራች ማህበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ አስገነዘቡ።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ለ15ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን 120 የህክምና ዶክተሮችን ዛሬ አስመርቋል።
በምረቃው መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ እንደገለፁት መንግሥት የጤና መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የህክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት በመስጠት ጤናማ አምራችና የበለጸገ ማህበረሰብ ለመፍጠር የህክምና ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዛሬዎቹ ተመራቂ የህክምና ዶክተሮችም የማህበረሰቡን ችግር በተገቢው በመረዳት በአገልጋይነት ስሜት አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ ተመራቂዎቹ ያስተማራቸውን ህብረተሰብ በቀናነት እና በታማኝነት ማገልገል ይገባቸዋል ብለዋል።
ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ተግባሩ ጎን ለጎን በሪፌራል ሆስፒታሉ ለበርካታ የሲዳማ እና አጎራባች ህዝቦች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሌጁ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ለማጠናከርና ለማስፋፋት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የኮሌጁ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር አለሙ ጠሚሶ በበኩላቸው ኮሌጁ ለጤና ዘርፉ መጎልበት እየተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት ከ2 ሺህ 300 በላይ የህክምና ዶክተሮችን በማስተማርና በማሰልጠን ወደ ስራው እንዲቀላቀሉ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው ዶክተር በረከት ዘላለም ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ላለፉት ሰባት ዓመታት በህክምናው ዘርፍ ያገኘውን እውቀት በስራ ለመተርጎም መዘጋጀቱን ተናግሯል።
ለዚህም ሳይማር ያስተማረውን ማህበረሰብ በማገልገል በጤናው ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ጉጉት እንዳደረበት አስታውቋል።
ሌላኛዋ ተመራቂ ዶክተር ቤተልሄም ደሳለኝ በበኩሏ የህክምና ትምህርት ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጻ በመምህራኖቿና ቤተሰቦቿ ጥረት በከፍተኛ ውጤት መመረቋን ገልጻለች።
በተለያዩ የህክምና ተቋማት በነበራት የትምህርት ልምምድ ወቅት የማህረሰቡን ችግሮች መረዳቷን ገልጻ የስራውን ዓለም ስትቀላቀል ህዝቡን በታማኝነት ለማገልገል በመዘጋጀት መሆኑንም አስረድታለች።