ቀጥታ፡

ሀገር አቀፍ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት"የጥራት መንደር" ዛሬ ይመረቃል

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዓመታት በፊት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት የተጀመረው ሀገር አቀፍ የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት፣ "የጥራት መንደር" ዛሬ እንደሚመረቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጥራት መንደር ቁልፍ ተቋማትን ያቀፈ መሆኑን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት ፣የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ከተቋሟቱ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን አመልክቷል።

ብሔራዊ የጥራት መሠረተ ልማት (NQI) የሀገሪቱን ደረጃዎች ልማት፣ የሥነ ልክ፣ የዕውቅና አሰጣጥ፣ የተስማሚነት ግምገማ፣ የገበያ ክትትል እና የጥራት ማስተዋወቅን በማጠናከር፣ ለንግድ ድርጅቶች የሚሰጠውን የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት ለማሳደግ ያለመ ነው።


 

በዘመናዊ መሳሪያዎች የተደገፈው እና የተሻሻለ አቅም ያለው 'የጥራት መንደር'፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር በተሻለ ሁኔታ እንድትሳለጥ፣ የቴክኒክ መሰናክሎችን እንድትቀንስ እና በዓለም አቀፍ ንግድ ያላትን ተሳትፎ እንድታሻሽል አጋዥ እንደሚሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም