ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል- ሚኒስትር ዴኤታ ሐሰን መሀመድ

ሐረር፤ ህዳር  14/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ  ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ ተናገሩ።

በሐረሪ ክልል በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ እየተከናወኑ በሚገኙ  ስራዎች ላይ ያተኮረ  ውይይት ተካሄዷል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ሀሰን መሀመድ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢንዱስትሪ ዘርፍ በአጭር ጊዜ መሠረታዊ የሆኑና ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

በተለይ የተዘጉ ኢንዱስትሪዎች ተከፍተዋል፤ የኢንዱስትሪው የማምረት አቅም ተሻሽሏል እንዲሁም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት የአምራች ኢንዱስትሪ ማነቆዎችን በመለየት  እንዲፈቱ አገዛ ማድረጋቸውን አንስተዋል።

አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ ፈጠራን በማበረታታትና ስራን የሚያቃልሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ አገሪቱ ከዘርፉ የምትጠብቀውን የወጪ ምርትን ከማሳደግና የገቢ ምርትን ከመተካት አንጻር አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።

ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን እንዲቀር እንዲሁም ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የታሰበውን የኢኮኖሚ ሽግግር ለማረጋገጥ መቻሉንም አንስተዋል። 

በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች የሚከናወኑ የኢትዮዽያ ታምርት ስራዎችን እንደ አገር አምስት ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ የክትትልና የድጋፍ ስራ በማከናወን ላይ መሆኑን ጠቁመው ይህም የአምራች እንዱስትሪ ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትና ውጤት እንዲያስመዘግብ ማድረጉን ተናግረዋል።

የመድረኩም ዓላማ  በክልሉ በኢትዮዽያ ታምርት ንቅናቄዎች ላይ የተከናወኑ ስራዎችን በመመልከት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ያለመ መሆኑን አመልክተዋል።

አምራች ኢንዱስትሪው አገር የምትጠብቀውን ውጤት እንዲያስመዘግብ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት፣ አዳዲስ እይታን ማስፋትና የተቀናጀ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ዘርፉ ጥራትን፣ምርታማነትንና መተማመንን የሚጨምሩ ስራዎችን በማዘመን ዓለም ዓቀፋዊ ተወዳዳሪነታቸውን የያዘ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል።


 

የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ዑመር በበኩላቸው በክልሉ በኢትዮዽያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ዘርፉን ለማዘመን ስትሪግ ኮሚቴ ተቋቁሞ  ወደ ስራ መገባቱን የጠቀሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ይህም ለስራው ተግባራዊነት ከፍተኛ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢስማኢል ዩሱፍ በበኩላቸው የኢትዮዽያ ታምርት በክልሉ በማንፋክቸሪንግና ቴክኖሎጂ፣ በጨርቃጨርቅ፣ በምግብና መጠጥ ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬ የማዳን ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ የአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቶች ከመሰረተ ልማት ጋር በተያያዘ የሚገጥማቸውን ችግሮች ከመፍታት አንጻር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አንስተዋል።

በውይይቱ ላይም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራር አባላትና የክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን በኢትዮዽያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ስራዎች ቀርበው ውይይት ተካሄዶባቸዋል።

 

 

  

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም