ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት ዘርፉ እንዲነቃቃ ያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ህዳር 14/2017(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማጎልበት ዘርፉ እንዲነቃቃ ማስቻሉን የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ገለጸ።

ባለፉት ዓመታት መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ለማረጋገጥ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማምጣት የተወሰደው የኢኮኖሚ የፖሊሲ ማሻሻያ ይጠቀሳል።

በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትግበራ በሁሉም መስክ ተጨባጭ ውጤቶች እንደተመዘገቡ ደግሞ ከሰሞኑ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ግምገማዎች ያሳያሉ።

ከማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው ትሩፋቶች መካከል አንዱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ዘላቂ ለማድረግ ወሳኝ ድርሻ ያለውን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማጎልበት መቻሉ ነው።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሰብስብ አባፊራ''የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉ ዘርፍ ለረጅም ዓመታት ሲናፍቀው የነበረ ነው'' ብለዋል።

የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ለሁሉን አቀፍ ልማት መረጋገጥ ያለውን አይተኬ ሚና በማውሳት፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ ያነቃቃና የዘመናት ጥያቄ የመለሰ ዕድል መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግሥት ብቻ የተያዙ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በሙሉና በከፊል ወደ ግል ለማዞር መወሰኑ አካታች፣ተወዳዳሪና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዕውን ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ሂደት የግል ዙርፉ የበኩሉን ወሳኝ አበርክቶ እንደነበረው አውስተው፤ በፍጆታና የግንባታ ዕቃዎች ሥርጭት ሂደት የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር መሥራቱን ለአብነት ጥቅሰዋል።

አገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በሚጠይቁ የወጪ ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በተደረገው ጥረት አምራች ኢንዱስትሪው ከመንግሥት ጋር በቅርበት ሲሰራ መቆቱን ተናግረዋል።

ገቢ ምርቶችና ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት ከዚህ በፊት የነበረው የውጭ ምንዛሬ ችግርም በማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራው እንዲቃለል በመደረጉ የግሉ ዘርፍ ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያው በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ የአሰራር ግድፈቶችን እየቀረፈ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚው ትግበራ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚጠይቅ በመግለጽ፤የግዙ ዘርፍ የነበረውን ትብብርና አገራዊ ኃላፊነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነትን ጨምሮ በተለያዩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድ ምህዳር ውስጥ ለመሳተፍ እያደረገች ባለው ጥረት ብርቱ ውድድር እንደሚጠይቅ አንስተዋል።

የግሉ ዘርፍ መጠናከር ደግሞ ለንግድ ውድድር ወሳኝ በመሆኑ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ለዘርፉ መነቃቃት ወሳኝ ድርሻ ያላቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም