የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ይጀምራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 14 /2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከኢትዮጵያ የ35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች መልስ ዛሬ በስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ወደ ውድድር ይመለሳል።
ፕሪሚየር ሊጉ ከጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ብሔራዊ ቡድኑ ከታንዛንያ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ተቋርጦ እንደነበር ይታወቃል።
ሊጉ ዛሬ በስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዳግም ሲጀመር ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
አርባምንጭ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።
በአሰልጣኝ በረከት ደሙ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ አራት ጎሎችን ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።
አርባምንጭ ከተማ በሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሊጉ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ተሸንፏል። ቡድኑ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር 10 ጎሎችን አስተናግዷል።
በጊዜያዊ አሰልጣኝ አታክልቲ በርሄ የሚመራው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ያለ ምንም ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃ ይዟል።
በሌላኛው የስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከድሬዳዋ ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃዋሳ ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።
በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ዘጠኝ ጎሎች ተቆጥረውበታል። በዘርዓይ ሙሉ የሚሰለጥነው ሃዋሳ ከተማ በሰባት ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባካሄዳቸው ስድስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
10 ግቦችን ሲያስቆጥር 8 ጎሎችን አስተናግዷል። በይታገሱ እንዳለ የሚመራው ድሬዳዋ ከተማ በስምንት ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ሲዳማ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰዓት፣ አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቀሌ 70 እንደርታ የስምንተኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።
የስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያሉ።
መቻል እና ወላይታ ድቻ በተመሳሳይ 13 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በአምስት ጎሎች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።
የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር እና ሌላኛው የቡድን አጋሩ ዩጋንዳዊው ቻርልስ ሙሲጌ፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራና የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ በተመሳሳይ አራት ግቦች ይከተላሉ።