የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በወንድማማችነት፣ በአብሮነትና በኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል - አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በወንድማማችነት፣ በአብሮነትና በኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል - አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በወንድማማችነት፣ በአብሮነትና በሕብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚገባው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
ለ19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ዝግጅት ስራ የተቋቋመው የጸጥታና ደኅንነት ንዑስ ኮሚቴ የስራ አፈጻጸም ግምገማ አፈ-ጉባዔው በተገኙበት ተደርጓል።
ንዑስ ኮሚቴው በቀጣይ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ዋና ዋና ጉዳዮችን የተመለከተ የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በግምገማው ወቅት በዓሉ ከጸጥታና ደኅንነት አንጻር በሰላም ለማክበር አጠቃላይ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በበቂ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተነስቷል።
አፈ-ጉባዔው ንዑስ ኮሚቴው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ኮሚቴው እስከ አሁን ያከናወነውን ውጤታማ የቅድመ ዝግጅት ሥራ በዓሉ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያና በአጠቃላይ በጸጥታና ደኅንነት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አካላት ድርሻ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በዓሉ በወንድማማችነት፣ በአብሮነትና በኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲከበር የሚሠራውን አጠቃላይ ተግባር በተገቢው ሁኔታ መደገፍ እንደሚገባም ነው አፈ-ጉባዔው ያሳሰቡት።
ዜጎች በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ለጸጥታና ደኅንነት አካላት ድጋፍ በማድረግ የተለመደ ትብብራቸውን እንዲያደርጉ አፈ ጉባኤው ጥሪ ማቅረባቸውን ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል "ሀገራዊ መግባባት ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ይከበራል።