በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ይደረጋል
ሆሳዕና ፡ ህዳር 13/2017(ኢዜአ):- በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ እንደሚያጠናክር የደቡብ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኩባንያ አስታወቀ ፡፡
የደቡብ ካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኩባንያ የቀድሞው የደቡብ ክልል የጋራ ሀብት ሲሆን ኩባንያው በ2007 ዓ.ም መመስረቱም ታውቋል።
ኩባንያው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ቅርጫፍ ፅህፈት ቤት ከፍቶ ዛሬ ስራ አስጀምሯል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊና የኩባንያው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በዚህ ወቅት እንደገለጹት ኩባንያው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ወጣቶችን በመደገፍ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚስተዋሉ የፋይናንስ ማነቆዎችን በመፍታት ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የስራ እድል ፈጠራን በማበረታታት ረገድ ተሞክሮ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በዚህም ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመረውን ጥረት ከግብ እንዲደርስ ከማድረግ አኳያ ዘርፉን ለማጠናከር ኩባንያው የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል፡፡
አዲስ በተደራጁት በ4ቱም ክልሎች የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በመክፈት የተቋሙን አገልግሎትና ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማስፈን እየተሰራ እንዳለ ጠቅሰው ሆሳዕና የተከፈተው ቅርንጫፍም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል ፡፡
ኩባንያው ለስራ አጥ ዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ያለውን አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡
የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታረቀኝ ባቼ በበኩላቸው ኩባንያው በ4ቱም ክልሎች በጥቃቅን፣ በአነስተኛና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ለተደራጁና 20 በመቶ ለቆጠቡት የማሽነሪ ሊዝ ፋይናንስ አገልግሎት እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በጨርቃ ጨርቅና በአልባሳት፣ በኮንስትራክሽን፣ በብረታ ብረትና በሌሎች ዘርፎች ለተሰማሩ ወጣቶች ከ408 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የማሽነሪ ብድር ማቅረቡን ተናግረዋል፡፡
በዚህም ከ12 ሺህ 700 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ሀብት እንዲያፈሩ የበኩሉን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው የቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን በማስፋት በክልሎቹ ለሚገኙ ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል ፈጠራን በማበረታታትና ቴክኖሎጂ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና እንደሚያጠናክርም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በመደገፍ ዘላቂ ኢኮኖሚን ከመገንባት አኳያ የኩባንያው ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት መከፈት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ደግሞ የክልሉ ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ ናቸው፡፡
በክልሉ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማ ከማድረግ አኳያ የሚስተዋሉ በርካታ ማነቆዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ኩባንያው ይህን በመፍታት ረገድ የላቀ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
ኩባንያው በኢንተርፕራይዞች ለሚነሱ የማሽነሪ ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት በክልሉ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልልና የዞን እንዲሁም የሆሳዕና ከተማና የኩባንያው ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡