ቀጥታ፡

የማኅበረሰቡን የጤና አገልግሎት ፍላጎት የማሻሻልና የማጠናከር ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦በማኅበረሰብ አቀፍ የጤና አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን የማሻሻልና የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት አስታወቀ።

ጤና መድህን ማለት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ አባል ወይም ቤተሰቦች የጤና
መታወክ ሲያጋጥማቸው የህክምና ወጪያቸው የሚሸፈንበት መንገድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት የ2017 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀሙን "የጤና መድህን አባልነት ለጋራ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።


 

በውይይት መድረኩ ላይ የፌደራልና የክልል ጤና መድህን ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ጤና መድህን ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የጤና መድህን ተጠቃሚ አባላትን ቁጥርን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

መድረኩ በዋናነት ፍትሃዊ የጤና አገልግሎትንና ጥራቱን የጠበቀና ዘላቂ የሆነ አገልግሎት አሰጣጥ ማሳደግ ላይ ማተኮሩን ተናግረዋል ፡፡

የጤና መድህንን በማጠናከር የሚፈለገውን የጤና አገልግሎት ለመስጠት በፌዴራል፣ በክልልና በዞን ደረጃ የጤና መድህን ቋት በማቋቋም እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

የጤና መድህን በዋነኝነት የሚያስፈልገው የህብረተሰቡን የመደጋገፍ ባህል ለማዳበር በመሆኑ አንዱ ወረዳ  ሌላውን ወረዳ ለመደገፍ እንዲችል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

በ2016 በጀት ዓመት 1 ሺ 52 ወረዳዎችን በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ከ53 ሚሊዮን በላይ አባላት ማፍራት መቻሉን ተናግረዋል።

ለዚህ ውጤት መገኘት መሰረቱ የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የሚመለከታቸው አጋርና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራታቸው ነው ብለዋል፡፡ 

በ2017 በጀት ዓመት ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ሥርዓት ትግበራ ለመጀመር የታሰበባቸውን ወረዳዎች  ለመለየት ለክልሎች ልዩ ድጋፍ መደረጉን ገልፀዋል።

በፀጥታ ችግር ምክንያት አገልግሎት አቋርጠው ለነበሩ ክልሎች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

በበጀት ዓመቱ በትግራይ 93፣ ሶማሌ 39፣ አፋር 18፣ ጋምቤላ 1 እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ 10 ወረዳዎች በአጠቃላይ አዲስ አባል የሚያፈሩ 160 ወረዳዎችን የመለየት ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል ።

መክፈል የማይችሉ ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

ለዚህም የህብረተሰቡን የገቢ መጠን መሠረት ያደረገ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን የመዋጮ ስርዓት ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

ከፍ ያለ ቋት መመስርት፣ አስፈጻሚ አካላትን ማጠናከር፣ መክፈል የማይችሉ ዜጎችን መለየትና የጤና  አገልግሎት አሰጣጥ ሥርአትን ማሻሻል የ2017 የትኩረት መስኮች እንደሆኑ  ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም