ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ “RELIEF” የተሰኘ ሕገወጥ መድኃኒትን ከመጠቀም እንዲቆጠብ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሕብረተሰቡ “RELIEF” የተሰኘ ሕገወጥ መድኃኒትን ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳሰበ።

ባለሥልጣኑ ሕገወጥ መድኃኒቱ (በውስጡ ዲክሎፌናክ፣ ፓራሲታሞል፣ ክሎረፊኒራሚን እና ማግኒዥየም ትራይሲሊኬት እንዳለው ይገመታል) በኢትዮጵያ ገበያ እየተዘዋወረ መሆኑን ባደረገው ክትትል እንደደረሰበት ገልጿል።

መድኃኒቱ በሕጋዊ መንገድ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያልተመዘገበ በመሆኑ ጥራቱ፣ ደህንነቱና ውጤታማነቱ እንደማይታወቅ አመልክቷል።

በተጨማሪም፣ የዚህ መድኃኒት የጎንዮሽ ጉዳቶች የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ ተቅማጥ፣ የሆድ ህመም፣ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ ድካም፤ የእይታ መዛባት፤ መፍዘዝ፣ ራስ ምታት፣ የቆዳ ሽፍታ፣ የጉበት ኢንዛይሞች መጨመርና ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሲውል የኩላሊት ጉዳትን እንደሚያስከትል አስታውቋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህንን መድኃኒት ለረጅም ጊዜ መጠቀም ከባድ የጉበት፣ የኩላሊት ጉዳት፣ የልብ ድካም እና ስትሮክ የመያዝ እድልን ከፍ ሊያደርግ እንደሚችልም ባለስልጣኑ አስጠንቅቋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ ይህንን መድኃኒት ከመጠቀም እንዲቆጠብ አሳስቧል።

ሕብረተሰቡ መድኃኒቱን በሚኖርበት አካባቢ ካገኘ በነጻ ስልክ ቁጥር 8482 ለኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለስልጣን ወይም ለክልል ጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲጠቁም ባለስልጣኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም