የቻይና ባለሀብቶች በመንግስት የእድገት ተኮር መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በትኩረት ይሰራል- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና ባለሀብቶች በመንግስት የእድገት ተኮር መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በትኩረት ይሰራል- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦ የቻይና ባለሀብቶች በመንግስት የእድገት ተኮር መስኮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።
አምባሳደር ምስጋኑ የኢትዮጵያ-ቻይና ወዳጅነት እና ትብብር ኮሚቴ ልዑካን አባላትን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ኮሚቴው የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።
በመንግስት የእድገት ተኮር መስኮች ተብለው ከተለዩት መካከል በማዕድን ዘርፍ የቻይና ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ይበልጥ መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበትን የቡና ምርት በተለየ ሁኔታ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም በቅርቡ የሚካሄደውን የሁለቱ አገሮች የባህል እና የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ኩነት ይበልጥ አጉልቶ መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ-ቻይና ወዳጅነት እና ትብብር ኮሚቴ ሰብሳቢ ቤቲ ሹው ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በነበራቸው የመስክ ምልከታ ያዳበሩትን የኢትዮጵያ እምቅ የኢንቨስትመንት እድሎች በማየት በቻይና ገበያ ለማስተዋወቅ እና የንግድ ትስስሩን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።
በተለይም በታዳሽ ኃይል አማራጭ ፣በማዕድን ዘርፍ ፣የኢትዮጵያ ቡና በመላክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ እንዲሆን የማስተዋወቅ እና ገበያ የማፈላለግ ስራዎችንም እንደሚከናውኑ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ይበልጥ በማጠናከር በልዩ ልዩ ዘርፎች በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ በመኪና እና የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ መገጣጠሚያ በኢትዮጵያ የመክፈት እቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ብዙ ቁጥር ያለውን የቻይና የቢዝነስ ድርጅቶችን ያቀፈው የኢትዮጵያ-ቻይና ወዳጅነት እና ትብብር ኮሚቴ ከወራት በፊት በኢትዮጵያ የመስክ ጉብኝት ማድረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።