ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት መሰጠቱ ተመለከተ

አሶሳ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦በቤኒሻንጉል ጉሙዝ  ክልል የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄን ውጤታማ   ለማድረግ  አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ ላይ ትኩረት መሰጠቱ ተመለከተ። 

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ  ያዘጋጀው  "የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ መድረክ በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ እንዳሉት፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መጠናከር ለክልሉ ብሎም ለአገር ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው። 

ለዚህም  ኢንዱስትሪዎችን በፋይናንስ፣ መሠረተ ልማት እና አደረጃጀት ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት አምራች ኢንዱስትሪው የሚኖረውን ፋይዳ በመረዳት የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍቶችን ማስተካከልና ለዚህም ተናቦ መስራት እንደሚገባ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።

የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ አመንቴ ገሺ በበኩላቸው፤  በክልሉ አምራች ኢንዱስትሪውን ለማነቃቃት  ዋነኛው ችግር ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር ነው ብለዋል።


 

በክልሉ 56 የሚደርሱ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ሆኖም  የሚጠበቅባቸውን ያህል እያመረቱ   አለመሆኑን ገልጸዋል።

የግብዓት እጥረት፣ የተመቻቸ የመሠረተ ልማት እንዲሁም የመሸጫ እና የመስሪያ ቦታ አለመኖር በክፍተትነት የጠቆሟቸው ናቸው።

ከፍተቶችን በማስተካከል በክልሉ የሚገኙትን ሀብቶችን እና የግብርና ምርቶችን በመጠቀም  የኢንዱስትሪዎቹን ምርታማነት ለማሳደግ   ትኩረት እንደተሰጠ  በመድረኩ ተገልጿል።

በንቅናቄ መድረኩ  የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የባንክና የፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎችን ና ሌሎች  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም