ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ141 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሯል

ደሴ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ  አራት ወራት ከ141 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች  የስራ እድል መፈጠሩን የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ አስታወቀ፡፡

በወሎ ዩኒቨርሲቲና አጋር አካላት አዘጋጅነት አለም አቀፍ የስራ እድል ፈጠራ ሳምንት በደሴ ከተማ ተከብሯል፡፡

የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ እንደገለጹት፤ በክልሉ ሀብትና ጸጋዎችን በመለየት ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ  የስራ እድል ለመፍጠር ከታቀደው ውስጥ ባለፉት አራት ወራት ከ141 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች   የስራ እድል ማመቻቸት መቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ውስጥ 51 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ማመቻቸት ተችሏል ያሉት አቶ አወቀ፤  ከ2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት በላይ ለመስሪያና መሸጫ ሼድ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

የስራ ዕድሉም  በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በግብርናና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሽዋዬ ታደሰ በበኩላቸው፤ በከተማው እስካሁን በተደረገ ጥረት ከአንድ ሺህ ለሚበልጡት የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ የበጀት ዓመቱ  እቅዱን ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና መምህር ዶክተር ይመር አያሌው እንዳመለከቱት፤  ዩኒቨርሲቲው በእውቀትና በቴክኖሎጂ የበለጸገ ስራ ፈጣሪ ትውልድ ለመገንባት እየሰራ ነው፡፡

ተግባር ተኮር ትምህርትና ስልጠና በመስጠትም ሰልጣኞች ስራ ጠባቂ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ በመሆን ኢኮኖሚውን ማነቃቃት እንዲችሉ ከአጋር አካላት ጋር በትብብር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

''በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ስልጠና ክህሎት መር ዜጋ ለመፍጠር እየተሰራ ነው'' ያሉት ደግሞ በደሴ ከተማ የወይዘሮ ስህን ፖሊ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ዲን አቶ ሰለሞን ይመር ናቸው፡፡

አለም አቀፍ የስራ ፈጠራ ሳምንት የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራር አባላት፣ ምሁራንና ሌሎችም  አካላት በተገኙበት በፓናል ውይይ ትመከበሩ  ተመልክቷል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም