ቀጥታ፡

የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ወደ ስራ ለማስገባት የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እየተከናወነ ነው

መቀሌ፤ ህዳር 13 /2017  (ኢዜአ)፦የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክን ሥራ ለማስጀመር የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፊልሞን ተረፈ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ ፊልሞን ተረፈ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ፓርኩን ወደ ስራ ለማስገባት የኢንተርኔት ኔትዎርክ መዘርጋት አንዱ ተግባር ነው።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ፤ ከኢትዮ ቴሌኮም ሰሜን ሪጅን ጋር በመነጋገር የመሥመር ዝርጋታ ሥራውን የማጠናቀቅ ተግባር ተከናውኗል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የፓርኩን የኤሌክትሪክና የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር ለመፍታት ያልተቆጠበ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል። 

በፓርኩ ውስጥ የውሃ አቅርቦት እንዲሟላ ኮርፖሬሽኑ 60 ሚሊዮን ብር ለመቀሌ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ክፍያ በመፈፀም የኮንትራት ውል የሚፈፀምበት ደረጃ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በኤሌትሪክ ሃይል በኩልም ከዚህ ቀደም ወደ ፓርኩ ተዘርግቶ የነበረው መስመር ከፍተኛ የሀይል መቆራረጥ ይታይበት እንደነበር አስታውሰዋል። 

ችግሩን ለመፍታት የሚጠቀምበትን የኤሌክትሪክ ሃይል የሚመጥን ሀይል ለማግኘት እንዲቻለው ኮርፖሬሽኑ 34 ሚሊዮን ብር ለመቀሌ የኤሌትሪክ ሃይል አገልግሎት ክፍያ መፈጸሙን አመልክተዋል። 

በመቀሌ ሳብስቴሽን የተፈጠረውን ችግር ለማቃለልም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም አቶ ፊልሞን ገልፀዋል። 

በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቀሌ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ግደይ በየነ ስለ ጉዳዩ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቀው ፖርኩ ያለበትን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ለማስቀረት ለመቀሌ ሰብስቴሽን በቀጥታ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ 34 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ገልፀዋል። 

መስመሩን ለመዘርጋት እንደ ገመድና የኮንክሪት ምሰሶ የመሳሰሉ ጥሬ እቃዎችን የማሰባሰብና ለስራው የሚሆን የሰው ኃይል የመመደብ ስራ ሲካሄድ መቆየቱንና የመስመር መዘርጋቱ ሥራ በቅርቡ ተጀምሮ በሁለት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙንም አቶ ግደይ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም