ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሮማንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር የማጠናከር ፍላጎት አላት- አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው

አዲስ አበባ ፤ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከሮማንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር የማጠናከር ፍላጎት እንዳላት በሮማንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፀጋአብ ክበበው ገለጹ።

አምባሳደር ፀጋአብ ከተለያዩ የሮማንያ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደሩ ከሮማንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ዳይሬክተር ቫለንቲን ቡዳ ጋር ባደረጉት ምክክር፥ የአገራቱን ለረጅም ጊዜ የቆየ ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን ተለዋውጠዋል።

በውይይቱ የኢትዮጵያና ሮማንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋማት የፖለቲካ ምክክራቸውን በድጋሚ ለመጀመር ከስምምነት ላይ ተደርሷል።

አምባሳደር ፀጋአብ ከሮማንያ የስራ እና ማህበራዊ ጥበቃ ሚኒስቴር የአውሮፓ ጉዳዮች እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ጀነራል ሊያና ሞስቴኔስኩ ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለትዮሽ የስራ ስምሪት ስምምነት በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ስራ እንዲገባ ተስማምተዋል።

በተጨማሪም አምባሳደሩ ከሮማንያ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ኦቪዲ ሎአን ሲላጊ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የሁለቱን አገራት የንግድ ምክር ቤቶች በማስተሳሰር የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ መጠን በማሳደግ የኢኮኖሚ ትስስሩን ማጎልበት እንደሚገባ ተነስቷል።

አምባሳደር ፀጋአብ በሮማንያ በነበራቸው ቆይታ የአራድ ከተማን የጎበኙ ሲሆን በከተማዋ ከሚገኙት የኢትዮጵያ የክብር ቆንስላ ሎን ሳንዱ ጋር ተወያይተዋል።

ፀጋአብ በክብር ቆንስላው ባለቤትነት የሚተደዳረውን “PAB” የተሰኘ የብረታ ብረት ማምረቻ ፋብሪካ ጎብኝተዋል።


 

አምባሳደሩ በአራድ የሚገኘው “University of Life Sciences” ባዘጋጀው ሁነት ላይ የኢትዮጵያ የግብርና እና ኢንቨስትመንት አቅም አስመልክቶ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ከከተማዋ ከንቲባና ሌሎች አመራሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል።

አምባሳደር ፀጋአብ ኢትዮጵያ ከሮማንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ትብብር የማጠናከር እንዲሁም በጋራ መልማትን ማዕከል ባደረገ መልኩ የግንኙነት አድማሷን ማስፋት እንደምትፈልግ መግለጻቸውን በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም