በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ ነው

ጂንካ፤ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
በምክትል ርዕሰ መስተደድር ማዕረግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ፣ በጂንካ ከተማ የኤሶል ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራቱን በማስጠበቅ ብቁ ዜጋ በማፍራት ረገድ ትልቅ ሚና እየተወጡ ይገኛሉ።
በወላይታ ሶዶ የሚገኘውን የሊቃ ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት በማሳያነት ጠቅሰው፤ ትምህርት ቤቱ በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተና ሁሉንም ተማሪዎች በላቀ ውጤት ማሳለፍ መቻሉ አስታውሰዋል።
እንደ ሊቃ ያሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ እና አቅም እያላቸው እድሉን ላላገኙ ተማሪዎች ትልቅ እድል በመሆኑ በክልሉ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋቱ ስራ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አታ በበኩላቸው የኤሶል ሁለተኛ ደረጃ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ለአካባቢው ትልቅ ዕድል ይዞ የመጣ ነው ብለዋል።
ትምህርት ቤቱ ተወዳዳሪ ተማሪዎች የሚፈልቁበት እንዲሆን በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራ ገልጸው ትምህርት ቤቱ የተጣለበትን ሀላፊነት እንዲወጣም ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
''ትምህርትን ያለ ህዝባዊ ድጋፍ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም'' ያሉት ደግሞ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳግም መኮንን፤ ትምህርት ቤቱ አደራውን በብቃት እንዲወጣ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ ባለድርሻ አካላት ተሳትፏቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።
የኤሶል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ባማልቆ ባዩ፣ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር የመማሪያ፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያና ሌሎች አገልግሎቶችን ምቹ የማድረግ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ ዘንድሮ በዞኑ በ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 50 ተማሪዎችን ተቀብሎ የመማር ማስተማር ስራ ላይ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል።
በክልል አቀፍ የ8ኛ ክፍል ፈተና 99 ነጥብ 86 በማስመዝገብ የኤሶል ሁለተኛ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤትን የተቀላቀለችው ተማሪ ቤተልሔም ሰለሞን፤ በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የመማር ዕድል በማግኘቷ መደሰቷን ገልፃለች።
''በቀጣይም ጠንክሬ በመማር ቤተሰቤንም ሀገሬንም ለማስጠራት ሙሉ ትኩረቴን በትምህርት ላይ አደርጋለሁ'' ብላለች።
የኤሶል ሁለተኛ ደረጃ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት በክልሉ በወላይታ ሶዶ ከሚገኘው ሊቃ፣ በጌዴኦ ዞን ከሚገኘው ደራሮ እና በጋሞ ዞን ከሚገኘው ባይራ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ቀጥሎ የተቋቋመ መሆኑ ታውቋል።