የሀገርና የክልሉን ኢኮኖሚ በማሳደግ የአምራችንና የቤተሰብን ህይወት በሚቀይር መንገድ መስራት ይገባል - ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር ኢ/ር)

አዲስ አበባ ፤ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦በኢንቨስትመንት መስክ የሀገርና የክልሉን ኢኮኖሚ በማሳደግ የአምራችንና የቤተሰብን ህይወት በሚቀይር መንገድ መስራት እንደሚገባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ።

በርዕሰ መስተዳድሩ የተመራ የፌደራል እና የክልል ልዑክ የብልጽግና ፓርቲ 5ኛ ዓመት ምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራን በማድረግ ጉብኝት አድርጓል።

በጉብኝቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሣ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

ጉብኝቱ በክልሉ በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ በሃ ቀበሌ በሃ ላንድ ቡና ልማት ድርጅት እያከናወነ ያለውን የስራ እንቅስቃሴ የተመለከተ ነው።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ካለው ሰፊ መሬቶች በግብርና ልማት ስራዎች በተለይም በቡና ፣በቅመማ ቅመምና በሰብል ልማት ዘርፎች በስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በክልሉ ቡና በስፋት የሚመረትና በዚህም የሀገርና የክልሉን ኢኮኖሚ በማሳደግ የአምራችንና የቤተሰብን ህይወት በሚቀይር መንገድ መስራት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።

በቡና ልማት ስራዎች በክልሉ በስፋት ተሰርቷል ያሉ ሲሆን፥ በየዓመቱ ከ70 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞችን በመትከል የቡና ማሳ ሽፋንን የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር በክልሉ በአማካይ 8 ኩንታል በሄክታር ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በበሃላንድ ቡና ልማት በሄክታር 14 ኩንታል ቡና መገኘቱ የሚበረታታና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው በበኩላቸው፥ በክልሉ ከ900 በላይ የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መኖራቸውንና ከዚህም ውስጥ 480 የሚሆኑት በቡና ልማት መሰማራታቸውን ተናግረዋል ።

በኢንቨስትመንት ከተያዙት 139 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥም ከ67 ሺህ በላይ ሄክታር የሚሆነው በቡና ልማት መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በክልሉ ከሚገኙ ኢንቨስትመንቶች አንዱ የሆነው በሃላንድ ቡና ልማት ድርጅት ከተረከበው 289 ሄክታር መሬት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው መልማት መቻሉ በተሞክሮነት የሚታይ መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም