ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ ሀብት በመጠቀም የአረንጓዴ ትራንስፖርት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሰራች ነው -አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ ሀብት በመጠቀም የአረንጓዴ ትራንስፖርት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሰራች ነው -አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ፤ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ያላትን እምቅ ሀብት በመጠቀም የአረንጓዴ ትራንስፖርት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
ኢትዮ ግሪን ሞቢሊቲ 2024 ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ሲምፖዚይም ዛሬ በአዲስ አበባ ተከፍቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዬ ታገሰ ጫፎ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት የአየር ንብረት ለውጥ እየፈጠረው ያለውን ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ መቋቋም የሚችል ዘላቂና አስተማማኝ አረንጓዴ ልማት መፍጠር ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ ሞቢሊቲን ሊደግፍ የሚችል እምቅ ታዳሽ ኃይል ባለቤት ናት ያሉት አፈ-ጉባዔው ይህን አቅም በመጠቀም የአረንንዴ ትራንስፖርት ፈር ቀዳጅ ለመሆን እየሰራች ነው ብለዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ አስመጪዎች የተለያዩ ማበረታቻ ድጋፎች እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ የበለፀገ ማህበረሰብ ለመፍጠር ፖሊሲ አውጪዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው አረንጓዴ ትራንስፖርት ኢትዮጵያ ዘላቂነት ያለው አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት አካል ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ማዕከልነቷን ለማስጠበቅ የተጀመሩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን በአረንጓዴ ትራንስፖርት ለመደገፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተሽከርካሪ መሰረተ ልማት ባለፈ የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን በማስፋት ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ፣የበካይ ጋዝን ለመቀነስና ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።
አውደ ርዕዩና ሲምፖዚየሙ እስከ ህዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።