ቀጥታ፡

በጎንደር ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል የኤሌክትሪክ አውቶብስ አገልግሎት ሊጀመር ነው

ጎንደር ፤ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፡- የጎንደር ከተማን የህዝብ ትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል 126 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገዙ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶብሶችን አገልግሎት ለማስጀመር መዘጋጀቱን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

የጎንደር ከተማ አስተዳደር በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ሦስት አውቶብሶችን ተረክቧል።

የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደተናገሩት፤ የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ አካባቢን የማይበክሉ የድምጽና የሞተር ጭስ አልባ በመሆናቸው ለከተማው ተመራጭ ቴክኖሎጂ ናቸው።

በአገሪቱ ከሚገኙ ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ጎንደር ከተማ አንዷ እንደመሆኗ ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ያስፈልጋታል፤ ለዚህም የአውቶብሶቹ ፋይዳ የላቀ ነው ብለዋል።

የከተማው ነዋሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚገጥማቸውን የትራንስፖርት እጥረት ለማቃለል የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ ሚናቸው የጎላ መሆኑን አስረድተዋል።


 

አውቶብሶቹ ለህብረተሰቡ የተሟላ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግም በተጠና አግባብ የስምሪት ቦታዎችንና የስራ ሰዓትን የመለየት ስራ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።

ከተማው ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ አውቶብስ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ምቹ ሁኔታ ለፈጠሩት ለአቶ በላይነህ ክንዴም ምስጋና አቅርበዋል።

የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካው ባለቤት አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው፤ ከጎንደር ሌላ ቀደም ሲልም ደብረብርሃን ከተማ የኤሌክትሪክ አውቶብስ ተጠቃሚ እንዲሆን ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል።

አውቶብሶቹ ወጪ ቆጣቢና ምንም ዓይነት የድምጽም ሆነ የጭስ ብክለት የማያስከትሉ ቴክኖሎጂዎች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ጎንደር የቱሪስት ከተማ እንደመሆኗ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ አንድ ጊዜ ባትሪያቸው ቻርጅ ከተደረጉ ለሶስት ቀናት ማሽከርከር እንደሚቻልና የመጫን አቅማቸውም 100 ሰው እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በኤሌክትሪክ አውቶብሶቹ የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) እና ሌሎችም የስራ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም