ቀጥታ፡

የቁም እንስሳትና ስጋ ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎች የዕርባታና ማድለቢያ ማዕከላት እንዲያዘጋጁ በትብብር እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

አዳማ ህዳር 13/2017(ኢዜአ)፤ የቁም እንስሳትና ስጋ ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎች ከመደበኛ ገበያ በተጨማሪ የራሳቸው የዕርባታና ማድለቢያ ማዕከላት በማዘጋጀት እንዲያደልቡ በትብብር እየተሰራ መሆኑ የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስጣኑ ወደ ውጪ የሚላክ ስጋ መጠን እንዲጨምር በዘርፉ ለተሰማሩ አካላት የአቅም ግንባታ ስልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በአዳማ አካባቢ የማድለቢያ ማዕከላት የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሃሚድ ጀማል (ዶ/ር) በተለይ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ወደ ውጪ የሚላክ ስጋ መጠን በማሳደግ ከእንስሳት ሀብት የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

የቁም እንስሳትና ስጋ የሚላከው ወደ መካክለኛው ምስራቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ሂደቱ የተቀባይ አገሮች ፍላጎትን ያሟላ መሆኑን የማረጋገጥ ስራም ትኩረት ማግኘቱን ተናግረዋል።


 

በዚህም የቁም እንስሳት ላኪዎችና የእንስሳት ስጋን ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎች የራሳቸው የዕርባታና ማድለቢያ ማዕከላት እንዲኖራቸው ለማስቻል አቅም ግንባታና ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለሙያዎች የእንስሳት ስጋን ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎችና የእንስሳት ማድለቢያ ማዕከላት ተመድበው አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ገልጸው፤ የእንስሳት ስጋን ወደ ውጪ የሚልኩ ከመደበኛ ገበያ በተጨማሪ በራሳቸው የዕርባታና የማድለቢያ ማዕከላት እንዲያደልቡ በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በዚህ ወቅት ካሉት 11 የእንስሳት ስጋን ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎች ሁለቱ የራሳቸው ማድለቢያ ከፍተው የእርድ እንስሳትን በሚፈለገው ብዛትና የክብደት መጠን እያደለቡ ስጋ ወደ ውጪ እየላኩ መሆኑንም ገልጸዋል።

በባለስልጣኑ የእንስሳት ምርት ጥራት ቁጥጥር መሪ ስራ አስፈፃሚ አያሌው ሹመት (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የጉብኝቱና የአቅም ግንባታው ዋና ዓላማ የቁም እንስሳትና የስጋ ወደ ውጪ መላክን ለማስተሳሰር ነው።


 

በጎች፣ ፍየሎች፣ ግመሎችና ሰንጋዎች የዓለም አቀፍ የገበያ ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ በሚፈለገው መጠን ለማቅረብ እንዲያመች ጭምር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ህገ ወጥ የእንስሳት ንግድ ለማስቀረት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አመልክተው፤ የእንስሳት ስጋ ወደ ውጪ የሚልኩ ቄራዎችና የቁም እንስሳት ላኪዎች ይሄንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በሙሉ አቅማቸው ሊሰሩ እንደሚገባም አሰገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም