የኢትዮጵያና የጣሊያንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚዲያና ኮሙንኬሽን ዘርፍ በትብብር መስራት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የጣሊያንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚዲያና ኮሙንኬሽን ዘርፍ በትብብር መስራት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና የጣሊያንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በትብብር መስራት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የጣሊያኑ የዜና ምንጭ 'አጀንዚያ ኖቫ' በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የታደሙት የሁለቱ ሀገራት አምባሳደሮች የአገራቱን ታሪካዊና ጠንካራ የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነት በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍም ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የጣሊያን አምባሳደር አጉስቲኖ ፓሌሴ፤ የኢትዮ-ኢጣሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በሁለቱም አገራት ቀዳሚ የሆኑት የሚዲያ ተቋማቱ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውም፤ የአገራቱን ወዳጅነትና የትብብር ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናከር ስለመሆኑ አንስተዋል።
የኢዜአ እና የአጀንዚያ ኖቫ የትብብር ስምምነትም የሁለቱን አገራት የመረጃ ልውውጥ በማጎልበት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጠናር ይሆናል ነው ያሉት።
የአገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የሚዲያ ትብብር በማጠናከር ረገድ ኤምባሲው እገዛ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ፤ የሁለቱ አገራት የልማት ትብብር ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን አንስተው፤ የኢዜአ እና የአጀንዚያ ኖቫ ስምምነትም ለሀገራቱ ጠንካራ ግንኙነት ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል።
የሚዲያ ተቋማቱ ትብብር የመረጃ ልውውጥ ከማጎልበቱ ባሻገር የሁለቱን አገራት ግንኙነት ይብልጥ የሚያሳድግ መሆኑንም አንስተዋል።
በጣሊያን ሮም የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለስምምነቱ ትግበራ ውጤታማነት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ሽብሩ ማሞ፤ ኢትዮጵያ ከኢጣሊያ ጋር ሁሉን አቀፍ የልማት ትብብሯን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
የሁለቱ ተቋማት ስምምነት የዓለም አቀፍ የሚዲያ አገልግሎት ልምድና ተሞክሮ ለመጋራት ብሎም ኢትዮጵያ በዓለም ሚዲያ ምህዳር ተደራሽነቷ እንዲጎለበት የሚያደረግ መሆኑንም አንስተዋል።
ሚዲያው በሀገራት የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ በተለይም ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ለማጠናከር ያለውን ወሳኝ ሚና በማውሳት፤ መግባቢያ ሰነድ ስምምነቱ ለሁለቱ ሀገራት ትብብርና መግባባት ይበጃል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ስምምነቱ በመረጃና ዜናዎች ልውውጥ እና በአቅም ግንባታ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
ኢዜአ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች ተደራሽነቱን በማስፋት በአፍሪካ ቀዳሚ የዜና ምንጭ ለመሆን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢጣሊያ አቻው ጋር መፈራረሙ ባለሙያዎቹን ለማሰልጠን እንደሚያግዘው ገልጸዋል።
በመረጃ ዘመን የሀገራት ትብብርና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጎልበት የሚዲያ ሚና ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ስምምነቱ በጋራ ጉዳዮች በትብብር ለመስራትና የተሻለ ነገ ለመገንባት ይረዳል ነው ያሉት።
የአጀንዚያ ኖቫ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፋብዮ ስኩላንቴ፤ ስምምነቱ የሁለቱን አገራት አጋርነትና ወዳጅነት ለማጎልበት የሚያግዙ ስራዎችን በጋራ ለመስራት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
አጀንዚያ ኖቫ ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱን ለማስፋት የሚያግዘው መሆኑን በመጠቆም፤ ከኢዜአ ጋር መፈራረሙ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በስምምነቱ መሰረት በመረጃ ልውውጥ በተለይም በዓለም አቀፍ ሁነቶችን በትብብር ተደራሽ ለማድረግ አስቻይ ዕድሎች ፈጥሮናል ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም ኢዜአ እና የጣሊያን ዜና አገልግሎት (ANSA) በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን በዛሬው እለት ከአጀንዚያ ኖቫ' ጋር የተደረገው ስምምነት ከኢጣሊያ ሚዲያዎች ጋር ሁለተኛው መሆኑ ነው።