ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው - ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦ ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ሲሉ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ሁለቱም የራሴ የሚሉትንም የጠላቴ የሚሉትንም በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወት አውሬ እንኳን በማይፈጽመው መልኩ በአስከፊ ሁኔታ በሁሉም አማራጮች ይገድላሉ ሲሉ አስፍረዋል።

ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግባር ይህንኑ የሚያመለክት ነው። ይህ ፈጽሞ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አፀያፊ ድርጊት መወገዝ አለበት ብለዋል።

ዓላማቸው ሁለት ነው። አንዱ ዓላማ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። በዚህም እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው። ሌላኛው ዓላማቸው በዚህ ኢሞራላዊ ድርጊታቸው በህዝብ ዘንድ ፍርሃት በማንገስ ያሻቸውን ማድረግ ነው ሲሉም ገልጸውታል።

ሁለቱም ሞታቸውን ያፋጥነዋል እንጂ የሚሳካ አይደለም። ቅዥት እና እኔ ብቻ የሚል ጫፍ የረገጠ ጽንፈኝነት የሚወልደው በመሆኑ እንዲህ አይነት እኩይ ፍላጎት መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን አይሳካም ብለዋል።

የአንድን ማህበረሰብ ልብ መግዛት የሚቻለው፣ በዚህም የትኛውንም አይነት ፍላጎት ከግብ ማድረስ የሚቻለው ምክንያታዊ በመሆን እና የማህበረሰቡን ህግጋትና ሞራላዊ እሴቶች በመጠበቅ ነው። ለማመን የሚከብድን ኢሞራላዊ ድርጊት በመፈፀም በዓለማችን የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የቆመለትን ግብ ያሳካ የለም። ለጊዜው አንዳንዶቹ ኢሞራላዊ ድርጊቶች አንድን ውጥን ያሳኩ ይመስሉ ይሆናል። ይህ እንዳልሆነ የፋሽስቶች ታሪክ ምስክር ነው ሲሉም አስፍረዋል።

በሁለቱም አቅጣጫ ሰሞኑን በሰላሌ ደራ ላይ የተፈፀመው አጅግ ሊወገዝ የሚገባው አይነት ሰውኛ ያልሆኑ ድርጊቶች በመፈጸም አማራና ኦሮሞን ለማጫረስ ያልተሞከረበት ጊዜ የለም። ግን ሁሉም አልተሳኩም ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነት ኢሞራላዊ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይሳካም ። ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሚዛናዊ፣ ትርፍና ኪሳራን ለይቶ በምክንያታዊነት አቋም የሚወስድና ወደ ድርጊት የሚገባ ነው በማለት ገልጸውታል።

ዶክተር ለገሰ ሸኔ እና ጽንፈኛው ጃውሳ በሚፈጽሙት አሠቃቂ ድርጊቶች ሁለቱን የተወለዱ፣ የተገመዱ፣ ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በመሆን በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ያፀኑትን ህዝቦች በማጋጨት የትኛውንም አይነት እኩይ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም ብለዋል።

የጽንፈኞች ፍላጎት ከማፍረስ እና ብጥብጥ ከመፍጠር የተሻገረ አይደለም ያሉት ሚኒስትሩ ፍላጎታቸው የህዝብ ጥቅም እና መብት ማስከበር ቢሆን ለምን ንጹሃንን ፣ ምስኪን፣ ራሳቸውን መካለከል የማይችሉ ሰዎችን ለምን ይገድላሉ ፣ ያርዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ሴቶች ይደፍራሉ፣ የህዝብና ግለሰቦች ሃብትና ንብረት ያወድማሉ? ዓላማቸው የራሳቸውን እና የሌሎች ሃይሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማገልገል ነው ብለዋል።

በእንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የተሰማሩትን አረመኔዎች መላው ህዝብ እና መንግስት በተባበረ ክንድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ስርዓት እንዲይዙ ያደርጋሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ይስተካከላል። እየነፈሰ ያለው ሰላምም ይፀናል በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም