በአፋር ክልል አርብቶ አደሩን በመረጃ የሚደግፍና የአደጋ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል አርብቶ አደሩን በመረጃ የሚደግፍና የአደጋ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
ሰመራ፤ህዳር 12/2017 (ኢዜአ)፦በአፋር ክልል አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን በመረጃ የሚደግፍና የአደጋ ተጋላጭነቱን ለመቀነስ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአፋር ክልል በሚገኙ 23 ወረዳዎች ላይ የአየር ጠባይና ሁኔታን ለመተንበይ የሚያስችል ዘመናዊ የቅድመ ትንበያ መሣሪያ ለመግጠም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
የኢንስቲትዮቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሳምነው ተሾመ በወቅቱ እንደገለጹት፥በክልሉ የሚከናወኑ የግብርና፣የአካባቢ ጥበቃና የመስኖ ስራዎችን በአየር ጠባይ መረጃ መደገፍ ላይ ተቋማቸው ትኩረት ሰጥቷል።
ፕሮጀክቱ በተለይም የአየር ሁኔታና ጠባይን ቀድሞ በመተንበይ የአደጋ ተጋላጭነትን የሚቀንስ መሆኑን ጠቁመዋል።
አክለውም፥ የግብርና ስራዎችን በተገቢው ለማከናወን መረጃን በቶሎ ከማድረስ አኳያ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል።
በኢንስቲትዩቱ የአፋር ክልል ሰመራ ማዕከል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰለሞን ቱሉ፥ ኢንስቲትዩቱ አርብቶ አደሩንና ከፊል አርብቶ አደሩን በአየር ትንበያ መረጃ ተጠቃሚ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
አሁን ላይ ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም የመረጃ ተደራሽነቱንና ተጠቃሚነቱን የሚያጠናክር መሆኑን አመልክተዋል ።
የክልሉ ቆላማ አካባቢዎች እና ኑሮ ማሻሻያ ኘሮጀክት አስተባባሪ ተወካይ አላዛር ይልማ በበኩላቸው፥በ23 ወረዳዎች ላይ የሚቋቋሙት ሰው አልባ የመረጃ መሠብሰቢያዎች አደጋ ከመከሰቱ ቀድሞ የቅድመ ማሥጠንቀቂያ ስራዎችን ለማከናወን እጅግ አጋዥ ናቸው ብለዋል።