ቀጥታ፡

በበጀት አጠቃቀምና ቁጥጥር ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ በመቀመር በደቡብ ሱዳን ፓርላማ ለመተግበር ተዘጋጅተናል --የደቡብ ሱዳን የፓርላማ አባላት

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦በበጀት አጠቃቀምና ቁጥጥር ኢትዮጵያ ያላትን ተሞክሮ በመቀመር በደቡብ ሱዳን ፓርላማ ለመተግበር መዘጋጀታቸውን የደቡብ ሱዳን የፓርላማ አባላት ተናገሩ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር እና የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ከደቡብ ሱዳን የፓርላማ ልዑክ አባላት ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊ አገር ለመሆን ስታደርግ የኖረችውን ጥረት ከመደገፍ ጀምሮ ለሁለንተናዊ ዕድገቷ ሚናዋን ስትወጣ መቆየቷ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ አገራት የጋራ የሆነ ሰፊ ድንበር የሚጋሩ፣ በህዝብ ለህዝብ ፣ በባህልና በአኗኗር በርካታ ትስስር እንዳለቸው ተነስቷል።

የደቡብ ሱዳን የፓርላማ ልዑካን የኢትዮጵያ ጉብኝት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀት አጠቃቀምና ቁጥጥር ልምድ ለመውሰድ ያለመ መሆኑ ተገልጿል። 


 

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺእመቤት ደምሴ (ዶ/ር) እንዳሉት ለልዑካኑ በበጀትና ፕላን ዙሪያ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።

ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ሪፎርምና እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች እንዲሁም የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ ማብራሪያዎች እንደተሰጣቸውም ተናግረዋል።

መሰል መድረኮች የሁለትዩሽ ግንኙነትን ለማጠናከር የሚያግዙ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።


 

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሙያዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሀፊ ንጉሴ መሸሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጎረቤት አገራትን ያስቀደመ መርህን በመከተል አፍሪካዊና ቀጣናዊ እድገትና የጋራ ልማት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

ለዚህም ወሳኝ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነት መሆኑን አንስተው የደቡብ ሱዳን ልዑካን በፓርላማ አሰራር ላይ ልምድ ለመውሰድ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ፓርላማ የበጀት አጠቃቀምና ቁጥጥር ተሞክሮ ለመውሰድ መምጣታቸውን የገለፁት ደግሞ የደቡብ ሱዳን ልዑካን ቡድን አባላት ናቸው።

በደቡብ ሱዳብ ፓርላማ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ፕላኒንግ አባል የሆኑት ዲንግ ላምዩኤልና ጎች ሞካች 15 አባላትን የያዘው የልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ ያለውን ተሞክሮ በመቀመር በደቡብ ሱዳን ፓርላማ ለመተግበር በማሰብ መምጣቱን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም