ቀጥታ፡

የአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም በአህጉሪቱ አካታችና ዘላቂ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓት ለመዘርጋት ሚናው የጎላ ነው - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦የአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም በአህጉሪቱ አካታችና ዘላቂ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ስርዓት መዘርጋት የሚያስችል መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

13ኛው የአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ስብሰባ "ዲጅታል አፍሪካን እውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ባለድርሻ አካላት መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የስብሰባው ዋነኛ ትኩረት ከኢትዮጵያ አካታችና ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ሽግግር ግንባታ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንተርኔት ለኢኮኖሚያዊ እድገት፣ ማህበራዊ ልማት፣ ለፈጠራ እንዲሁም ትምህርት  እና ጤና አገልግሎት ተደራሽነት ወሳኝ ሚና እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡

የአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ፎረም በአህጉሪቱ ተገቢና ትክክለኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ለመስጠት፣ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል ለመገንባት እንዲሁም የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካን ኢኮኖሚና ዜጎችን ከሳይበር ጥቃት ለመከላከልና ደህንነቱ የተጠበቀና ቀጣይነት ያለው የዲጂታል መሰረተ ልማት መገንባት እንደሚገባም ተናገረዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በማስፋፋት፣ የዲጅታል ፈጠራን በማበረታታት ተጨባጭ እርምጃ ወስዳለች ብለዋል፡፡ 

በመሆኑም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኢንተርኔት አስተዳደር ትግበራ እና የዲጂታል ሽግግር እውን መሆን በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ክላቨር ጋቴቴ በበኩላቸው የዲጂታል መዋቅራዊ ሽግግር ለሁለንተናዊ እድገት መሰረት መሆኑን አንስተዋል።

በአፍሪካ እንደ ሞባይል ገንዘብ መተግበሪያ ባሉ አገልግሎቶች በዓመት እስከ 919 ቢሊዮን ዶላር ማንቀሳቀስ ተችሏል ብለዋል፡፡

በአንጻሩ ከ800 ሚሊየን በላይ አፍሪካውያን የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ደህንነት እና የመረጃ ሉዓላዊነት ሥጋት በአህጉሪቱ ቀጣይነት ያለው የዲጂታል ሥነ ምህዳር ልማት ፈተናዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ 

በመሆኑም የአፍሪካን የዲጂታል ቴክኖሎጂ እና ዲጅታል ሽግግር እውን ለማድረግ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም