ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መውሰድ የምንችለው በግብርና እና ሌሎች የልማት መስኮች የጀመርናቸውን ሥራዎች በማጠናከር ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መውሰድ የምንችለው በግብርና እና በሌሎች የልማት መስኮች የጀመርናቸውን ሥራዎች በማጠናከር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው በሰላም ተምሳሌቷና ጎተራዋ ሙሉ በሆነችው ደጀን ወረዳ ባየነው የጤፍ ክላስተር ልማት ተደንቀናል ሲሉ አስፍረዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ መውሰድ የምንችለው በግብርና እና ሌሎች የልማት መስኮች የጀመርናቸውን ሥራዎች በማጠናከር ነው ብለዋል።


 

ለዚህም እንደ ሀገር ለክላስተር ግብርና የሰጠነው ትኩረት ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ትርፍ አምራች ከሆኑ አካባቢዎች አንዱ በሆነው ምስራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ የተመለከትነው ጤፍን በክላስተር የማልማት ሥራ የሚደንቅ ነው ብለዋል።

በዘንድሮ የመኸር እርሻ ለግብዓት አቅርቦትና ለዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠታችን ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ተዘዋውረን የተመለከትነው የሰብል ቁመና ያሳያል ያሉት አቶ ተመስገን በቀጣይም ለመስኖ ልማት እና ለሰላም ትልቅ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።

ማህበረሰቡም የሰላምና የልማት አርበኝነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው የምስራቅ ጎጃም ዞን ህዝብ በተለይም የደጀን ወረዳና አካባቢዋ ነዋሪዎች ላሳዩን ድንቅ የጤፍ ልማትና ላደረጉልን ደማቅ አቀባበል ከልብ እናመሰግናለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም