የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሐን ላይ የሚፈጽሙትን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አወገዘ

ህዳር 12/2017(ኢዜአ)፦ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች በንጹሀን ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት አወገዘ።

የአሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ ሀይሉ አዱኛ በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በክልሉ ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ በጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ የሚወገዝ ድርጊት ነው ብለዋል።

የሸኔ አሸባሪ ቡድንና ጽንፈኛው ፋኖ የተለያየ ቋንቋ ይናገሩ እንጂ ድርጊታቸው ተመሳሳይ መሆኑን ገልጸው፤ እነዚህ ቡድኖች በህዝቡ መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር አስነዋሪ ድርጊቶችን እየፈጸሙ መሆኑን ተናግረዋል።

አሸባሪው የሸኔ ቡድን በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሚፈጽመው ድርጊት የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ እንዲወድቅና ልማት እንዲደናቀፍ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

ጽንፈኛው ፋኖ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በንጽሀን ላይ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን በመግለጫቸው አንስተዋል።

የክልሉ መንግስት በቡድኖቹ የሚፈጸመውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በማውገዝ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ የህግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ከፌዴራል የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን በአሸባሪው ሸኔ ላይ ተከታታይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም መንገድ የመረጡት የቡድኑ አባላት እጃቸውን እየሰጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ህዝቡ እነዚህ ቋንቋቸው እንጂ ተግባራቸው አንድ የሆነ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖችን ለማስወገድ በጋራ እንዲቆም መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም