የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በዘርፉ ለሀገርና ህዝብ የሚበጅ ጠንካራ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በዘርፉ ለሀገርና ህዝብ የሚበጅ ጠንካራ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለሀገርና ህዝብ የሚበጅ ጠንካራ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በበኩሉ ረቂቅ አዋጁ በነጻነትና በተጠያቂነት ሚዛኑን የጠበቀ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን አስታውቋል።
የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የህዝብ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩም የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት፣የሙያ ማህበራት፣ የሲቪክ ማህበራት እና የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ተሳትፈዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዮናታን ተስፋዬ፤ የረቂቅ አዋጅ ማሻሻያውን አስፈላጊነት በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ለህዝብና ለመንግስት ጥቅም እንዲሁም ለሚዲያው ዘርፍ ዕድገት የሚበጅ ሆኖ ማሻሻያው ስለመዘጋጀቱ አንስተዋል።
ከሁለት ዓመታት በፊት በአዋጅ በቁጥር 1238/2013 የጸደቀው የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ለሚዲያ ተቋማትና ለሙያ ማህበራት ማስፋፋት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት እንዲቋቋም ስለማድረጉ አስታውሰዋል።
አዋጁ በባለስልጣኑ አደረጃጀት፣ የቦርድ አወቃቀር፣ ምልመላ፣ ስልጣንና ተግባር ባለስልጣኑ የተሰጠውን ተልዕኮ እንዳይወጣ እንከን የፈጠሩ ድንጋጌዎችን የያዘ እንደነበር ግን አንስተዋል።
በመሆኑም የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት ባለስልጣኑ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት፣ ውጤታማ ቁጥጥርና የማስፈጸም አቅም እንዲኖረው የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በማሻሻያው ሀገርና ህዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ ይዘቶችን መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን አንስተው በሂደቱ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ሊያጠቡ የሚችሉ ጉዳዮች እንዳይኖሩ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።
ከሚዲያ ባለሙያዎችና የህዝብ ውክልና በሚያረጋግጥ መልኩ ብዝሃነትና ገለልተኝነት በተጠበቀ አግባብ መሻሻል ስላለበት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል ከሚዲያ ተቋማት የክስ ሂደትና ቅሬታ አቀራረብ፣ የሚዲያ ካውንስል ድጋፍና አስቻይ ምህዳር ከመጠበቅ አኳያ መካተት አለባቸው የሚሉትን ሃሳቦች በመጥቀስ በቀጣይ ተጨማሪ ውይይቶች እንዲደረጉም ጠይቀዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፤ የረቂቅ ማሻሻያው አስፈላጊነት ጠንካራ አስፈጻሚ ተቋም ለመገንባት እና በነጻነትና በተጠያቂነት ሚዛኑን የጠበቀ አሰራር ለመዘርጋት መሆኑን ገልጸዋል።
ለህዝብ ሰላምና ለሀገር ደህንነት ቅድሚያ በሰጠ አግባብ መሻሻሉ አስፈላጊ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬከተር ዮናታን ተስፋዬ፤ ነገን የሚሻግር ጠንካራ አስፈጻሚ ተቋም ለመገንባት፣ የሚዛን መዛባትን ለማረምና የህዝብን ጥቅም ለማስጠበቅ ማሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቴ አለነ፤ የመገናኛ ብዙሃን ረቂቅ አዋጅ ለሀገርና ህዝብ የሚበጅ ጠንካራ የአሰራር ስርአት ለመዘርጋት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም በመድረኩ የተነሱ ሃሳቦችን ቋሚ ኮሚቴው ወስዶ በራሱ ሕጋዊ አሰራር መሰረት እንደሚመለከት ገልጸዋል።
በነጻነትና በተጠያቂነት ሚዛኑን የጠበቀ፣ ለህዝብ ጥቅም የቆመ፣ የመንግስት ህፀጽ በመንቀስ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የሚበጅ ጠንካራ ሚዲያ መፍጠር ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።
በጉዳዩ ላይ ሃሳብ ማጋራት የሚሹ ወገኖችም በተለያዩ አማራጮች ለቋሚ ኮሚቴው ማቅረብ እንደሚችሉ ጠቁመው እንደ አስፈላጊነቱ ቀጣይ ውይይቶች ሊደረጉ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።