የኢትዮጵያ አካታች የምጣኔ ሃብት መርሃ ግብር በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አካታች የምጣኔ ሃብት መርሃ ግብር በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አካታች የምጣኔ ሃብት መርሃ ግብር በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገለጸ።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በተገኙ ውጤቶችና በምጣኔ ኃብታዊ ሽግግር ዙሪያ ከልማት አጋሮች ጋር በዛሬው እለት የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በኢንቨስትመንት አማራጮችና ማበረታቻዎች፣ አካታች ምጣኔ ሃብት ለመገንባት በተያዘው አቅጣጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይቱ ተሳታፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
በፓናል ውይይቱ የተሳተፉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችም በኢንቨስትመንት፣ ንግድና ሌሎች ዘርፎች የተደረጉ የማሻሻያ ስራዎችና የቀጣይ የትብብር መስኮችን በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና አካታች ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እያከናወነቻቸው ስላሉ ተግባራት አብራርተዋል።
ሀገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ መርሃ ግብር ጥራትና አካታችነት ያለው ኢኮኖሚ ለመገንባት መሆኑን ጠቅሰው በዚህም ባለፉት አምስት አመታት በቤተሰብ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው የፋይናንስና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት በማምረቻው ዘርፍ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አንስተው በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ማሻሻያው ምላሽ ማግኘቱን ገልጸዋል።
በማምረቻው ዘርፍ በኢንዱስትሪ ፓርክ ለሚያመርቱ ኢንቨስተሮች ያገኙትን የውጭ ምንዛሬ መጠቀም የሚችሉበት የተለየ እድል መሰጠቱንም አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ ሪፎርሞች ያመጡት ለውጥ የምጣኔ ሃብት ሪፎርሞች ዘላቂ ምጣኔ ሃብት እድገት ለማምጣት መሰረት የሚሆኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር)፤ በብዝሃ ምጣኔ ሃብት ዘርፍ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም በአረንጓዴ አሻራ፣ በግብርና፣ በከተማ ልማትና ሌሎች ዘርፎችም ተጨባጭ ውጤት እያመጣች መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድረግ የረዥም፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ እቅዶችን በመንደፍ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።