ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠው የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ስልጠና ሀገርን ለሚጠብቅ ሰራዊት የበለጠ አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠው የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ስልጠና ሀገርን ለሚጠብቅ ሰራዊት የበለጠ አቅም የሚፈጥር ነው
አዲስ አበባ፤ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሰጠው የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ስልጠና ሀገርን ለሚጠብቅ ሰራዊት የበለጠ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ገለጹ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በመተባበር በሳይበር ጥቃት መከላከል ያሰለጠናቸውን የመከላከያ ሰራዊት አባላት አስመርቋል።
በምረቃ ስነ- ስርዓቱ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትእግስት ሀሚድ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና ሌሎች ጥሪ የደረገላቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ኢትዮጵያ የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጠብቅ ጀግና ሰራዊት ያላት አገር ነች።
ስልጠናው የአገር መከላከያ ሰራዊት እውቀትና ክህሎትን መሰረት ባደረገ መንገድ ሀገርን ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ የሚያደርገውን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
መከላከያ ሰራዊት የአገርን ሉዓላዊነት የሚጠብቅ መሆኑን በመግለፅ ለአባላቱ የተሰጠው ስልጠናም ሀገርን ለሚጠብቅ ሰራዊት የበለጠ አቅም የሚፈጥር እንደሆነ ገልፀዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትግስት ሀሚድ በበኩላቸው፤ የሳይበር ጥቃት በመከላከል የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
የሳይበር ጥቃትን ለመከላከልና የመረጃ የበላይነትን ለማረጋገጥ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት፣ የሰው ሃይል አቅምን በማጎልበትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ረገድ በስፋት መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም ሀገርን ከሳይበር ጥቃት በመከላከል ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።
የሳይበር ደህንነትን መጠበቅ ለሀገር እድገት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ሁሉ ሳይበርን ለህገወጥ ተግባር በሚያውሉ አካላት የሚደርሰው ጉዳትም ከፍተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።
በመሆኑም የሀገርን ድጂታል ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የፀጥታና ደህንነት ተቋማትን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ገልጸው፥ ለዚህም የትብብር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።