ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገነባበት መድረክ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የሚገነባበት መድረክ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ በህዝቦች አንድነት እና መቀራረብ ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ ተካሒዷል።

መድረኩ "ሀገራዊ መግባባት፤ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሔደ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እና በጨፌ ኦሮሚያ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር በዚሁ ወቅት፤ የህዝባዊ ውይይቱ ዋና አላማ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን በማጠናከር በህዝቦች መካከል መቀራረብን ማጎልበት ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓልን ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠርና አንድነትን ለማጽናት በሚያስችል አግባብ ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የለውጡ መንግስት የነበሩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣትና ደረጃ በደረጃ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ሐቀኛ የፌደራል ስርዓት እንዲጠናከር እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ብዝሃነታችን ጸጋችን፤ ባህሎቻችን ደግሞ መድመቂያዎቻችን መሆናቸውን በመረዳት እየተገነባ ላለው እውነተኛ ፌደራሊዝም ስር መስደድ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ነው ያሉት።


 

የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ሰዓዳ አብዱራህማን በበኩላቸው፤ ህብረ ብሔራዊ አንድነት የተረጋገጠባት እና የተሻለች ሀገር ለመገንባት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስትም ሰላምና ደህንነትን በማረጋገጥ ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ሁሉንም ዜጎች ባሳተፈ መልኩ እየሰራ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት።

በህብረ ብሔራዊ አንድነት ሀገር መገንባት ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው ያሉት አፈጉባዔዋ የለውጡ መንግስት እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲገነባ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የተሳተፉት ወይዘሮ ጸሐይ ኃይሉ መንግስት ባለፉት ስድስት ዓመታት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ የሰጠበት አግባብ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ የመድረኩ ተሳታፊ ወይዘሮ ሰሚራ መሐመድ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ለህብረ ብሄራዊ አንድነት መጎልበት ቁልፍ ሚና እንዳለው አንስተዋል።

አቶ ኤሊያስ አለማየሁ በበኩላቸው ህብረብሔራዊ ፌደራሊዝም ስር እንዲሰድ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በአርባ ምንጭ ከተማ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም