ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ሽግግር መሳካት አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ገለጹ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ለኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ሽግግር መሳካት አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የተለያዩ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋማት ተናገሩ።

በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው በተገኙ ውጤቶችና በምጣኔ ኃብታዊ ሽግግር ዙሪያ ከልማት አጋሮች ጋር ምክክር ተካሂዷል።

በመድረኩ ኢትዮጵያ እየተገበረቻቸው ያሉ ፓሊሲዎች፣ የተገኙ ውጤቶች፣ በቀጣይ የተያዙ እቅዶችን በተመለከተ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፃ አድርገዋል።

በመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝምና በዘላቂ የልማት ግቦች በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶችንና  የልማት አጋሮች እገዛ የሚያስፈልግባቸው ክፍተቶችን በተመለከተም አብራርተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎችም ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በማክሮ ኢኮኖሚ እንዲሁም በምጣኔ ኃብታዊ ሽግግር አጀንዳ እያከናወነች ያለውን ስራ አድንቀዋል።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ አስተባባሪ (ዶ/ር) ራሚዝ አላክባሮቨ፤ ኢትዮጵያ የያዘችው የፖሊሲና እስትራቴጂ አቅጣጫ ዘላቂ ልማትን እውን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይ በዲጂታልና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በታዳሽ ሃይል፣ በስርአተ ምግብና ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት በትብብር ለመስራት ዝግጁ ስለመሆናቸውም አረጋግጠዋል።


 

የካናዳ የልማት አጋር ድርጅቶች ምክትል ሊቀመንበር አይሻ ሙልሮኒይ በበኩላቸው 35 የልማት አጋሮችን በውስጡ የያዘው የካናዳ የልማት አጋር ድርጅቶች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መስራቱን ይቀጥላል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት መርሃ ግብር ሃላፊ ሳሙኤል ዱኢ፤ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የምጣኔ ሃብት ሪፎርም ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑ እየታየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት የሚከናወኑ ተግባራትን በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በመደገፍ ትብብራቸውን እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በተመሳሳይ የምጣኔ ሃብት ሽግግርን የሚያፋጥኑ የሙያ ድጋፎችና ሌሎች ዘርፎች ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ በአምራች ዘርፍ፣ በግብርና፣ በአገልግሎትና በንግድ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ያነሱት ደግሞ በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ቪናያክ ናጋራጅ ናቸው። 

ቀጣናዊና አለም አቀፋዊ የምጣኔ ሃብት ትስስርን ለማጠናከር እያከናወነች ያለው ተግባርም የሚበረታታ እንደሆነ ጨምረዋል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ የኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ሽግግር ሂደት ላይ የልማት አጋሮች እያደረጉ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አካታችና ሁሉን አቀፍ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት የማክሮ ኢኮኖሚው ትግበራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በኢንቨስትመንትና የልማት ትብብር ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት ዘርፉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንደኛው ትኩረት በመሆኑ በሎጅስቲክስና ሌሎችም አማራጮች መሳተፍ የሚቻል መሆኑንም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመሰረተ ልማትና የምጣኔ ሃብት ትስስር ለመፍጠር እያከናወነች ያለው ጥረትም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም