ብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር በመፈጸም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር በመፈጸም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ብልጽግና ፓርቲ ቃልን በተግባር በመፈጸም የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ተጠናቋል።
በመድረኩም አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ የዋናው ጽህፈት ቤት፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት እንደ ፓርቲ የተከናወኑ ተግባራት አፈጻጸም የተገመገመ ሲሆን፤ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ተቀምጧል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፤ የፓርቲው የሩብ ዓመት ግምገማ በተሳካ ሁኔታ መከናወኑን ተናግረዋል።
በየጊዜው ራሱን በአግባቡ እያስተማረና እያደገ የሚሄድ ፓርቲ መሆን፤ የመንግስት አቅዶችን በብቃት መፈጸምና የክትትልና ድጋፍ ስርዓትን ማጠናከር የፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤትና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተልዕኮዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህን መሰረት በማድረግም በሩብ ዓመቱ በፓርቲው የተከናወኑ ስራዎች ላይ ጥልቅ ግምገማ ተደርጓል፡፡
በዚህም በሩብ ዓመቱ እንደ ገዥ ፓርቲ ቃልን በተግባር ለመፈጸም የሚያስችሉ ውጤታማ የንቅናቄ ስራዎች በማከናወን በእቅድ የተያዙ ስራዎችን ማሳካት ተችሏል ነው ያሉት።
ለአብነትም በግብርና በጤና እና ሌሎች ማህበራዊ ዘርፎች እንዲሁም በፖለቲካና ጸጥታ ስራዎች ለውጥ ተመዝግቧል ብለዋል።
ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ተግባራትን በፍጥነት ከማከናወን አኳያም እመርታ ታይቷል ብለዋል።
ፓርቲው በአጭር ጊዜ ለ14 ሚሊዮን አባላትና አመራሮቹ ስልጠና መስጠት መቻሉን ጠቅሰው፤ የአሰራር ስርዓቶችንም በፍጥነት በማጠናቀቅ ተግባራዊ ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡
በሁሉም የፓርቲው መዋቅሮች መካከል የተቀራረበ የአፈጻጸም አቅም እየተገነባ መምጣቱንም ነው የተናገሩት።
ባካሔድናቸው ውይይቶች ልምዶችና ተሞክሮዎችን ከመቅሰም ባሻገር በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የተሻለ መግባባት ፈጥረናል ሲሉም ተናግረዋል።
በቀጣይም ሁሉንም ስራዎች በጥራት መስራት እንዲሁም የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ተቋማዊና ስርዓታዊ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
አመራሩ የህዝብን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ መስራትና መደገፍ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ተጠያቂነት ባረጋገጠና ሁሉን ባሳተፈ መልኩ ሥራን በትግል መምራት የቀጣይ አቅጣጫ መሆኑንም ነው አቶ አደም ፋራህ የተናገሩት።