የደሴ ከተማ አስተዳደር ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
የደሴ ከተማ አስተዳደር ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል

ደሴ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ የደሴ ከተማ አስተዳደር ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው ገለጹ።
የደሴ ከተማ አስተዳደር የስራ እድል ፈጠራ እንቅስቃሴ የንቅናቄ መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው አስተዳደሩ ለስራ እድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለዚህም ሀብትና ጸጋዎችን በመለየት ለስራ እድል ፈጠራ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በበጀት ዓመቱ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ስራ አጥነትን ለመቀነስ በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ሽመልስ አመልክተዋል፡፡
በደሴ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አራት ወራት ከ2ሺህ 600 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የከተማው ስራና ስልጠና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት፤ በከተማው የወጣቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ ለሚበልጡ ዜጎች በተለያየ ዘርፍ የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ባለፉት አራት ወራት ከ2ሺህ 600 ለሚበልጡ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
የሥራ ዕድሉም በማምረቻ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በግብርናና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥ 92 በመቶው ቋሚ መሆኑን ጠቁመው የስራ እድል ለተፈጠረላቸው ዜጎች 38 ሚሊዮን ብር ብድር ከማመቻቸት ባለፈ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች እየተዘጋጁላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመድረኩ የከተማ፤ የክፍለ ከተማና የቀበሌ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።