ኢትኖ ማይኒንግ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ያስገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትኖ ማይኒንግ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ያስገኛል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ ኢትኖ ማይኒንግ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ከማስገኘቱም በላይ በሕገወጥ የማዕድን ሥራ ለተጋረጠው ፈተና ምላሽ ይሰጣል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ኢትኖ ማይኒንግ የአኮቦ ሚኒራልስ ኩባንያ መጋቢ ሲሆን በስካንዲኔቪያን ሀገራት መሠረቱን ያደረገ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ወርቅ ፍለጋ እና ማውጫ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ በተደረገው በዚህ ትርጉም ባለው ኢንቨስትመንት ሁላችንም እንኳን ደስ አለን ለማለት እንፈልጋለን ብለዋል።
ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በአኮቦ የምትገኘው ዲማ ከተማ በአነስተኛ ባሕላዊ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሂደት ላይ ብዙውን ጊዜ ብክነት የተሞላበት አሠራር በተግባር የተቆየባት ከተማ መሆኗንም ጠቅሰዋል።
ይኽ አዲስ ኢንቨስትመንት በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት ከማስገኘቱም በላይ በሕገወጥ የማዕድን ሥራ ለተጋረጠው ፈተና ምላሽ እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
ከዚህም ባሻገር ለጋምቤላ ክልል ዘላቂ ልማት በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ለሕዝቡ እና ለክልሉ ጠቀሜታ የማዋል ያለውንም ተነሳሽነት እንደሚያሳይም አመላክተዋል።