ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው እዳ እንዳይኖር በትጋትና ቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው እዳ እንዳይኖር በትጋትና ቁርጠኝነት እየተሰራ ነው - ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11/2017(ኢዜአ)፦ ለቀጣዩ ትውልድ የምናወርሰው እዳ እንዳይኖር በትጋትና ቁርጠኝነት እየተሰራ ነው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግስት በተለይም ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር እውን መሆን የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ ለሀገራዊ እድገትና ዘላቂ ልማት መሳካት የላቀ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መንግስት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግርን የተሳካና የተሳለጠ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን ከነበረባት የውጭ የእዳ ጫና ለማውጣት ባለፉት ስድስት ዓመታት የ10 ቢሊዮን ዶላር እዳ ክፍያ መፈፀሙን ገልጸዋል።
በዚህም የኢትዮጵያን የውጭ እዳ ጫና ከ30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 13 ነጥብ 7 በመቶ ማውረድ መቻሉን ነው የተናገሩት።
የሰፋ የልማት እቅድ ላላት ኢትዮጵያ በዚህ ልክ የእዳ ቅነሳ ማድረግ ማለት ትልቅ ትርጉም አለው ሲሉም አስረድተዋል።
በቀጣይ ለትውልድ የምናወርሰው ምንም አይነት እዳ እንዳይኖር መንግስት በትጋትና ቁርጠኝነት እየሰራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ጠንካራ ዓላማና እቅድ በመሰነቅ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማትና ብልጽግና ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ባለፉት ስድስት ዓመታት የእዳ ክፍያ ከመፈፀም ባለፈ ከውጭ ምንም አይነት የንግድ ብድር አለመወሰዱንም ተናግረዋል።
የእዳ ጫናውን ከማቅለል ባለፈ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የእዳ ሽግሽግ መደረጉንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ2050 በዓለም ግዙፍና ያደገ ኢኮኖሚ ካላቸው 20 አገራት መካከል ለመሆን ራዕይ አስቀምጣ እየሰራች መሆኑ ይታወቃል።