ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ ናት - አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

4ኛው የኢትዮጵያ እና የአውሮፓ ሕብረት የጋራ የሥራ ቡድን ስብሰባ ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተካሂዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ ሕብረት ወሳኝ ስትራቴጂክ አጋር መሆኑን በመግለጽ ኢትዮጵያ ከሕብረቱ ጋር ውጤታማ ተሳትፎ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ ሀገር መሆኗን በማንሳት የፍልሰት ጉዳይ ጥንቃቄ ከሚሹ የፖለቲካ ጉዳዮች ጋር እኩል ሚዛን የሚሰጠው መሆኑን አምባሳደር ምስጋኑ አንስተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት የፍልሰትን ችግር ከስር መሰረቱ ለመቅረፍ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን መከላከልን ጨምሮ የተቀናጀ ጥረት እያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ፍልሰት እና ከፍልሰት ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ግንኙነት ከጎረቤት ሀገራት እና ከዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኑን ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በፍልሰት እና ፍልሰት ጉዳይ ከሕብረቱ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ጠቁመዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ የአውሮፓ ሕብረት ከአሁን በፊት በኢትዮጵያውያን ላይ ያሳለፈውን የቪዛ እገዳ ለማንሳት የተግባር እንቅስቃሴ ማድረግ እንደሚገባው መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም