በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና እድገትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የጃፓን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - አምባሳደር ሺባታ ሒሮኖሪ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና እድገትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የጃፓን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - አምባሳደር ሺባታ ሒሮኖሪ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና እድገትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የጃፓን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሒሮኖሪ ተናገሩ።
የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የተመሰረተበት 70ኛ ዓመት እና የጃፓን በጎ ፈቃደኞች ትብብር በኢትዮጵያ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የጀመሩበት 50ኛ ዓመት በአዲስ አበባ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ኢትዮጵያና ጃፓን ከ80 ዓመታት በላይ የዘለቀው ጠንካራ ትብብር በየጊዜው እየጎለበተ መምጣቱ ተገልጿል፡፡
በተለይም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ እና የበጎ ፈቃደኞች ህብረት በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና ዕድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተነስቷል።
አምባሳደር ሺባታ ሒሮኖሪ አገራቸው ባለፉት 50 ዓመታት ለኢትዮጵያ ያላትን አጋርነት ሳታቋርጥ መቀጠሏን ጠቁመዋል፡፡
በግብርና፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲሁም በካይዘን ፍልስፍና ትግበራ በአነስተኛ ወጭ ብዙ ምርት እንዲመረት ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትና እድገትን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በተለያዩ ዘርፎች እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡ ከ700 በላይ የጃፓን በጎ ፈቃደኞች እንዳሉ አንስተው ይህም የአብሮነትና የትብብር ግንኙነትን የሚያጠናከር ተግባር መሆኑን አንስተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለሰ መኮንን (ዶ/ር)፤ ጃፓን ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች የኢትዮጵያ ጠንካራ የልማት አጋር መሆኗን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ዘላቂ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡
የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በአየር ንብረት፣ ምግብ ዋስትና እና ኢንሹራንስ ለአርሶ አደሮች የሚያደርገው ድጋፍ ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧልም ብለዋል፡፡
በግብርና በተለይም የሩዝ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያደርገውን ድጋፍ ጨምሮ በዘጠኝ ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጄ፤ የጃፓን በጎ ፈቃደኞች በኮሚኒኬሽ ስትራቴጂ ላይ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
የየካቲት 12 ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተባባሪ ዮዲት ተፈራ እና የኢየሩሳሌም ቅደመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ዓለምእሸት አዲሱ፤ የጃፓን በጎ ፈቃደኞች ለተማሪዎች በተግባር የተደገፈ ትምህርት እየሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በጎ ፈቃደኞች በአካባቢው የሚገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ተማሪዎች ትምህርታቸውን በቀላሉ የሚረዱበት ስልት በመቀየስ በትምህርት ፍላጎታቸው ላይ መነቃቃት ፈጥረዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያና ጃፓን የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ1930ዎቹ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።