ለዘላቂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ያስፈልጋል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ - ኢዜአ አማርኛ
ለዘላቂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ትብብር ያስፈልጋል - የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦ ዘላቂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ማረጋገጥ የሚቻለው ገበያን እና የግሉን ዘርፍ የሚደግፍ መንግስት እና ከመንግስት ጋር የሚተባበር የግል ዘርፍ መገንባት ሲቻል መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለጹ።
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ውጤቶችና ዘላቂ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር የሚኖረውን ፋይዳ አስመልክቶ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በነበሩ መንግስታት የተተገበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የየራሳቸው ውጤቶች እንደነበራቸው አስታውሰዋል።
በሂደቱ ኢትዮጵያን ለዘላቂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያላበቁ በመሆናቸው ወደ ተማሏ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ሳትሸጋገር መቆየቷን ጠቅሰዋል።
ኢኮኖሚ በመንግስት ቁጥጥር ስር ብቻ ወይም የመንግስት ሚና የሌለበት የግል ዘርፍ ብቻ ከሆነ የኢኮኖሚ ሸግግር ሊረጋገጥ እንደማይችል ገልጸዋል።
በዚህም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሸግግርን ለማረጋገጥ የግሉን ዘርፍና ገበያን የሚደግፍ መንግስት እና ከመንግስት ጋር የሚተባበር ጠንካራ የግል ዘርፍ መገንባት ይገባል ነው ያሉት።
የሀገርን ዘላቂ እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረተ ልማት፣ ቴክኖሎጂ መር ሰብዓዊ ልማት እና የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም መንግስት በሀገራዊ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ኢንቨስትመንት ማፍሰሱን እንዲሁም በገንዘብና ፊሲካል አስተዳደር የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ማድረጉን ጠቅሰዋል።
መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ ለግሉ ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ስራዎች ማከናወኑን አንስተዋል።
ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መካከል የዋናው እና የትይዩ ገበያ የውጭ ምንዛሬ በማመጣጠን መረጋጋት መፍጠሩን አስታውሰው፤ በቀጣይም ይህ ውሳኔ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የውጭ ምንዛሬ ማቅርብ ለምርትና ምርታማነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የማሰባሰብ አማራጮችን እንዲያሰፉ አሳስበዋል።