ኢዜአ ለኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ ለኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/ 2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የመረጃ ተደራሽነትን ውጤታማ ለማድረግ ለኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ነጋሲ አምባዬ ገለጹ።
ኢዜአ ከተለያዩ የፌዴራል ተቋማት ለተውጣጡ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው በአምስት ርእሰ ጉዳዮች ላይ ማለትም በኮሙኒኬሽንና ስትራቴጂ፣ በመልዕክት ቀረጻ እና በንግግር ፅሁፍ አዘገጃጀት፣ በግራፊክስና አኒሜሽን፣ በምስልና ድምፅ ቀረፃ እንዲሁም በምስልና ድምፅ ቅንብር ላይ ያተኮረ ነበር።
ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው ለስልጠናው ተሳታፊዎች የምስክር ወረቀት በሰጡበት ጊዜ እንደገለጹት ስልጠናው የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በእውቀትና በክህሎት የተሟላ አቅም እንዲፈጥሩ በማድረግ ሀገራዊ ተልዕኮዎችን ተረድተው የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
ያገኛችሁትን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር በቀጣይ ስራችሁ የመረጃ ተደራሽነትን ውጤታማ በማድረግ እንደ ሀገር የተጣለባችሁን ሃላፊነት ልትወጡ ይገባል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቀጣይም ኢዜአ የመረጃ ተደራሽነትን ውጤታማ ለማድረግ ለተቋማት የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች የሚሰጠውን ስልጠና አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የስልጠናው ተካፋይና በመከላከያ ሚዲያ ስራዎች ዳይሬክቶሬት የጋሻ ጋዜጣ ትምህርትና መዝናኛ አዘጋጅ ሻምበል ሰለሞን ሁነኛው ስልጠናው የመንግስትን ፖሊሲና ስትራተጂ ተገንዝቦ በኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ዘርፍ ተገቢውን ሥራ ለመሥራት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
እንደ ተቋም የኮሙኒኬሽን ስራችንን በአግባቡ ለመስራት ትልቅ ጠቀሚታ አለው ያለው ደግሞ ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌታቸው ረቢራ ነው።
በስልጠናው ያገኘውን እውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የተቋሙን የመረጃ ተደራሽነት ውጤታማ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በስልጠና ምክርና ምርምር ማዕከሉ ለተቋማት የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች ከሚሰጠው ሙያዊ ስልጠና ባለፈ የህትመት አገልግሎትና ጥናቶችንም ያከናውናል።