የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሃገራዊ ምክክር ሂደት ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በሃገራዊ ምክክር ሂደት ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦በሃገራዊ ምክክር ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን አካሄዷል።
ምክር ቤቱ በጠቅላላ ጉባዔው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የመከረ ሲሆን አካታች ሃገራዊ ምክክር አጀንዳ መለየትን በተመለከተ በሃገራዊ ምክክር ሒደት በመሳተፍ የበኩሉን ሚና ሲወጣ መቆየቱን አስታውቋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በጉባዔው ላይ የ2016 ዓ.ም የስራ ክንውን ሪፖርት እና የ2017 ዓ.ም የስራ እቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
ጉባዔው የጋራ ምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማፅደቁንም ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አካታች ሃገራዊ ምክክር አጀንዳ መለየትን በተመለከተ የጋራ ምክር ቤቱ በሃገራዊ ምክክር ሒደቱ ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ሚና ሲወጣ መቆየቱ በጉባኤው ላይ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት መመስረቻ ቃል ኪዳን መሰረትም በተለይ የጋራ ምክር ቤቱን ዓላማ የሚመለከቱ አጀንዳዎች ከፖለቲካ ፓርቲዎች በማሰባሰብና በተለያየ ጊዜ በመገናኘት ያዳበሩትን በማጠቃለል የቀረቡ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት ለሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዲቀርብ በሙሉ ድምጽ ወስነዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በጉባኤው በያዘው አጀንዳ መሰረት የቀጣይ የስራ ዘመን እቅድ ዝርዝር በመመልከትና በማዳበር ያጸደቀ ሲሆን የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁም ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ የጋራ ምክር ቤቱ ባካሔደው ጉባኤ በነባሩ ስራ አስፈጻሚ ምትክ አዲስ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ መምረጡንም ገልጿል።
በዚህ መሰረትም የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ሰለሞን አየለ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር አብዱልቃድር አደም (ዶ/ር) የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ሆነዋል።
እንዲሁም አቶ ደስታ ዲንቃ ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ ) ዋና ፀሐፊ፣ ወይዘሮ ሂንዲያ ሻፊ ከጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መርጧል።
አቶ ካህሳይ ዘገዬ ከአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ፣አቶ አውግቸው ማለደ ከቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ፣ አቶ መለሰ ዓለሙ ከብልጽግና ፓርቲ በጋራ ምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ ምክር ቤቱን በቅርበት ሲያግዙ ለቆዩ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት በመስጠት ጉባኤውን አጠናቋል።