የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በ615 ወረዳዎች ተጠናቋል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ - ኢዜአ አማርኛ
የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በ615 ወረዳዎች ተጠናቋል - ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/2017(ኢዜአ)፦ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በ615 ወረዳዎች መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፤ የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በተሳካ መልኩ ቀጥሉ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም በቅንነትና በንቃት እንዲሳተፍ አስገንዝበዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ መደበኛ ስብሰባው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የምክክር ሂደቱ የደረሰበትንና ባለፉት ሶስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በ9 ክልልችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በ615 ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
ከአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት በኋላ ለሚካሄደው ብሔራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችም የመምረጥ ስራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የምክክር ሂደቱን ለማስጀመር ከክልል አመራሮችና በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ የፌደራል ተቋማትና የዳያስፖራ አጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ያልተካሄደባቸው አካባቢዎች የማካሄድ ስራ የቀጣይ ትኩረት ይሆናሉ ብለዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ እያካሄደ ያለው ምክክር የሚበረታታ መሆኑን ጥያቄና አስተያየት የሰጡ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ በቀረው ጊዜ ስራውን ለማጠናቀቅ ያለውን ዝግጁነት፣ የታጠቁ ሃይሎችንና ፖለቲኞችን በምክክሩ ተሳታፊ በማድረግ ረገድ ያለውን ሁኔታም የምክር ቤቱ አባላት ጠይቀዋል።
የምክክር ሂደቱ ሁሉንም አካታች፣ ግልጽና አሳታፊ ሆኖ እንዲቀጥል እየሰሩ መሆኑን የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በምላሻቸው አስረድተዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ እንደየአካባቢው ሁኔታ የአካታችነት ጉዳይ በጥንቃቄ አየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የምክክር ሂደቱ አካታች በሆነ መልኩ በመደማመጥና በመግባባት እንዲካሄድ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር)፤ መንግስት ለዘመናት የቆዩ ችግሮችን በንግግር የመፍታት ጽኑ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላም ለማጽናት በሚደረገው ጥረት የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለግጭት፣ ልዩነትና አለመግባባት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና ሀገረ-መንግስትን ለማጽናት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ለምክክር ሂደቱ መሳካት ሁሉም በንቃትና በቅንነት እንዲሳተፍ አስገንዝበዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት ምክር ቤቱ በሁሉም ረገድ አስፈላጊውን ክትትል፣ እገዛና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።