በክላስተር ከለማው የመኸር ወቅት ስንዴ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - ኢዜአ አማርኛ
በክላስተር ከለማው የመኸር ወቅት ስንዴ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን

አዲስ አበባ፤ ህዳር 10/ 2017 (ኢዜአ):- በክላስተር ከለማው የመኸር ወቅት ስንዴ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን ሲሉ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በወረዳው የሌማት ትሩፋት ፕሮግራም ተግባራዊ በመደረጉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ምንጭና ለሥርዓተ-ምግብ መሻሻል የራሱን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝም ተመልክቷል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደሮች እንደገለጹት፤ በ2016/17 የመኸር እርሻ ስንዴን በክላስተር እንድናለማ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።
አርሶ አደር አቶ ተፈሪ ዓለሙና አቶ አደፍርስ አርጋው የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች አስፈላጊ የግብርና ግብዓቶች ያለምንም ችግር በወቅት መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
የግብርና ባለሙዎችም በየጊዜው ሙያዊ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው አመላክተዋል።
እኛም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታና ሙያዊ እገዛ መሰረት ስንዴን በክላስተር አልምተናል ብለዋል።
ከዚህ የክላስተር ልማትም የተሻለ ምርት እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል።
በዶሮ እርባታ የተሰማሩት አቶ ሔኖክ ደምሰው በዘርፉ ውጤታማ ሥራዎች እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሞረትና ጅሩ ወረዳ የሰብል ልማት አስተባባሪ አቶ ካሱ አበበ፤ በወረዳው የማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘርና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችም በወቅቱ እንዲሰራጭ መደረጉን ጠቁመዋል።
የሞረትና ጅሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ገድሉ ካሳው በበኩላቸው፤ ሞረትና ጅሩ በእንስሳት እርባታና በሰብል ልማት ለክልሉ ትልቅ አቅም የሚሆን ወረዳ ነው ብለዋል።
በ2016/17 የመኸር ወቅት በክልሉ ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በዘር ተሸፍኗል ያሉት ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ናቸው።
ከዚህም 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በሞረትና ጅሩ በመስክ ምልከታ ወቅት የታየው የክላስተር እርሻ የታቀደውን እቅድ በትክክል ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።