በአማራ ክልል በገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ስራ ማህበራትን ለመፍጠር የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ስራ ማህበራትን ለመፍጠር የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ነው
ባህር ዳር፤ ህዳር 10/2017 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በኢኮኖሚ አቅማቸው የጠነከሩና በገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የህብረት ስራ ማህበራትን በማደራጀት ለህብረተሰቡ ቀልጣፋ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የክልሉ ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት የህብረት ስራ ማህበራት ሪፎርም የንቅናቄ መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
የባለስልጣኑ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ የዝና ደስታ እንደገለፁት፤ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችሉ የህብረት ስራ ማህበራትን ማደራጀት ለነገ የሚባል ተግባር አይደለም።
በክልል ደረጃ ከ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሏቸውና በተለያየ ዘርፍ የተደራጁ 76 ዩኒየኖችና ከ29 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት እንደሚገኙ ተናግረዋል።
እነዚህ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች በኢኮኖሚና በሰው ኃይል አደረጃጀት ጠንካራ ሆነው እንዲወጡ የሪፎርም ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ሪፎርሙም ደከም ያሉና የተበታተኑ ማህበራትን ወደ አንድ በማሰባሰብ ጠንክረው እንዲወጡና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ያለመ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
የአስተዳደሩ አመራሮችም ህብረት ስራ ማህበራት የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት መሆናቸውን በመገንዘብ ጠንክረው ወደፊት እንዲመጡ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የህዝብ ግንኙነትና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጊዜው ታከለ በበኩላቸው፤ ህብረት ስራ ማህበራትን ሪፎርም ማድረግ የተቀላጠፈ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።
አስተዳደሩም ባለፈው ዓመት 60 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር መድቦ የፍጆታና የሰብል ምርቶችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ ገበያው እንዲረጋጋ ማድረጉን አመልክተዋል።
መደራጀታቸው ለህብረተሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ማህበራቱ በኢኮኖሚ ጠንክረው እንዲወጡ የተጀመረውን የሪፎርም ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በከተማ አስተዳደሩ 121 የህብረት ስራ ማህበራት ተደራጅተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ማህበራት ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ወርቁ ናቸው።
በመሆኑም የተበታተኑ ማህበራትን በማሰባሰብ በኢኮኖሚ ጠንክረው በመውጣት ለሸማቹ ህብረተሰብ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።
''ሪፎርሙ በተደራጀ መንገድ ውጤታማ አገልግሎት እንድንሰጥ ያግዘናል'' ያሉት ደግሞ የፈለገ አባይ ሸማቾች ዩኒየን ሰብሳቢ አቶ ቻለው አላምኔ ናቸው።
በዚህም ምርትን በብዛትና በጥራት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ ድርሻው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
የልደታ ሸማቾች ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ውብርስት እንዳለው በበኩላቸው፤ሪፎርሙ ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም በመፍጠር የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
በመድረኩ ላይም የክልል፣ የከተማ አስተዳደሩና የህብረት ስራ ማህበራት አመራር አባላትና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።